ቀጥታ፡

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪ ርዝራዦችን ለቅመው ለመደምሰስ ወደ ዘመቻው አቀኑ

አሶሳ፤ ሕዳር 15 / 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአሸባሪውን ህወሓት ተላላኪ ርዝራዦችን ሙሉ ለሙሉ ለቃቅሞ ለመደምሰስ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተደራጅተው ወደ ዘመቻው አቀኑ።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ኢስሃቅ አብዱልቃድር ዛሬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ክልሉ  የአሸባሪው ህወሓት የጥፋት ግንባር ሆኖ ቆይቷል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላም የአሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎች እና ቅጥረኞች የህዳሴው ግድብ መገኛ የሆነው የመተከል ዞን ለዓመታት የዘለቀ ግጭት ቀጠና እንዲሆን ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡

ኅብረተቡን በመከፋፈል ማጋጨት ደግሞ የአሸባሪው  ቡድኑ በመላላክ የጥፋት ተልዕኮ አስፈጻሚዎች የተከተሉት እኩይ ተግባር እንደነበር አውስተው፤ የሰዎች ህይወት እና ንብረት ሲጠፋ  በርካቶች መፈናቀላቸቀውን ጠቅሰዋል፡፡

የክልሉ መንግስት እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚመራው የመተከል ኮማንድ ፖስት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ሠላም ለመመለስ እልህ አስጨራሽ ስራ ሲያካሂዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

የሃገር መከላከያ ሠራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝን ጨምሮ የተለያዩ ክልሎች ልዩ ሃይሎች የህይወት መስዋዕትነት ጭምር መክፈላቸውን ጠቅሰው፤ የዞኑ ነዋሪዎችም መረጃ ከመስጠት ጀምሮ ተደራጅተው አካባቢያቸውን በመጠበቅ ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን አብራርተዋል፡፡

በዚህም በአሁኑ ወቅት የመተከል ዞን ወደ ተሻለ መረጋጋት እንደተመለሰ አቶ ኢስሃቅ ተናግረዋል፡፡

ነዋሪዎች በሰላም ወጥተው ከመግባት ጀምሮ ግብይት እና የእርሻ ስራዎቻቸውን ተረጋግተው ማከናወን ጀምረዋል ብለዋል፡፡

ይህ ያልተመቸው የአሸባሪው  ህወሓት ቡድን   ሰሞኑን በመተከል ዞን አልመሃል ጠርፍ አካባቢ ተላላኪዎቹን በማስገባት   የማተራመስ ሙከራ ማድረጉን አሰታውሰው፤ በጸጥታ ሃይሎች ተገቢውን ቅጣት ተቀብሎ መመለሱን ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮያውያን ጦርነት  ሰልችቷቸዋል የሚሉት አቶ ኢስሃቅ፤ የውክልና ጦርነቱን ለማክሸፍ  በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ወንድም ኤርትራዊያንም ጭምር መነሳታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመታቸው ተከትሎ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ከአሸባሪው ህወሃት ተላላኪ ርዝራዦች  ሙሉ ለሙሉ ለማጽዳት ተደራጅተው ወደ ክልሉ ግንባር ዘመቻ ማቅናታቸውን አቶ ይስሃቅ ለኢዜአ አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ የግጭት ታሪክ እንዲዘጋ የድርሻችንን ለመወጣት ቆርጠን ተነስተዋል ብለዋል፡፡

የአጎራባች ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች እና በየደረጃው የሚገኘው የጸጥታ መዋቅር ጋር በተናበበ መልኩ እየሠራን ነው ያሉት፡፡

የአሸባሪውን ተላላኪዎች ከክልሉ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የማጽዳት ስራ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ ሀገርን የማዳን ወሳኝ ጉዳዮችን መሠረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በክልሉ የአሸባሪው ቡድን ተላላኪ  ርዝራዦችን ከማስወገድ ባለፈ በአማራ እና አፋር ክልሎች የሚካደውን የህልውና ዘመቻ የሚሳተፉበትን ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑን አቶ ኢስሃቅ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም