የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ተከትለው ሊዘምቱ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ተከትለው ሊዘምቱ ነው
ህዳር 15 ቀን 2014(ኢዜአ) የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ተከትለው ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ፡፡
የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ጉዳይ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
መግለጫውን የሰጡት የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ እና የእናት ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አቶ ጌትነት ወርቁ፤ "ኢትዮጵያን እስከ ሲኦል ሔደንም ቢሆን እናፈርሳለን" በማለት የጋራ ቤታችንን ለመበታተን የተነሳውን የህወሃት አሸባሪ ሃይል ጊዜ ሳይሰጡ ማስወገድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም የየፓርቲዎቹ አመራሮች ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ተከትለው ወደ ግንባር ለመዝመት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
"አገር የህልውና አደጋ ተጋርጦባት ሳለ የምንሰስተውና ለነገ የምንለው ህይወት የለንም፡ ስለሆነም በግንባር ተገኝተን ለመፋለም ተዘጋጅተናል" ነው ያሉት።
አሸባሪው ህወሃት በወረራ በያዛቸው አካባዎች ሁሉ ንጹሃንን በመግደል፣ ከቤት ንብረታቸው በማፈናቀል፣ በመዝረፍ፣ ሴቶችን በመድፈር በኢትዮጵያ ታሪክ "አስከፊ ጥፋት" ሊባል የሚችል ዘግናኝ ግፍ አድርሷል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የጥፋት ቡድኑን እኩይ ድርጊት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስቆም ሁላችንም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ ተከትለን መዝመት ግድ ይለናል ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ ዋና ሰብሳቢ እና የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ምክትል ፕሬዘዳንት ሙሉጌታ ወርቁ በበኩላቸው ኢትዮጵያን አሸባሪው ከተጋረጠባት የህልውና አደጋ ለማዳን የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳላቸው ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉብንን ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን የህልውና አደጋ በጋራ ለመመከት ለመዝመት ወስነናል ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሌሎች እንዲዘምቱ ከመቀስቀስ ባሻገር ግንባር ድረስ በመሔድ ለተከታዮቻቸው አርአያ መሆን እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
ወቅቱ ሁሉም ሰው ኢትዮጵያዊነቱን ከቃል በዘለለ በተግባር የሚያረጋግጥበት እንደሆነም ተናግረዋል።
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ "ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ፤ ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሱ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ!" ማለታቸው ይታወቃል።