መሪዬ ወደ ግንባር ሲያቀኑ ዘመቻውን እንድቀላቀል በመጠራቴ እድለኛ ነኝ - ኢዜአ አማርኛ
መሪዬ ወደ ግንባር ሲያቀኑ ዘመቻውን እንድቀላቀል በመጠራቴ እድለኛ ነኝ
ሐረር፤ ህዳር 15 ቀን 2014(ኢዜአ) መሪዬ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ግንባር ሲያቀኑ ዘመቻውን እንድቀላቀል በመጠራቴ እድለኛ ነኝ ይላሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል።
የአስር አለቃ መኮንን ሰዒድ በሐረር ከተማ ሸንኮር አካባቢ የቀበሌ 09 ነዋሪ ናቸው።
የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባል የነበሩ ሲሆን፤ ከኢትዮ -ሶማሊያ ጦርነት ጀምሮ ለ15 ዓመታት እግረኛ ጦር ሆነው የሀገራቸውን ሉአላዊነት በመጠበቅ ስራ ላይ ተሰማርተው አገልግለዋል።
ከዛም መለስ በሐረር ማርሽ ባንድ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች በመሆን ያላቸውን እውቀት ለህዝብ በማካፈል ሲሰሩ እንደቆዩ ነው አስር አለቃ መኮንን ለኢዜአ የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅትም መንግስት ለቀድሞ የጦር ሰራዊት ባቀረበው ጥሪ ግንባር ቀደም ሆነው ምዝገባ ማካሄዳቸውን ይገልጻሉ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት በሚካሄደው ዘመቻ እንዲቀላቀሉ በመጠራታቸው የተሰማቸው ደስታ ከፍተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።
መሪዬ ወደ ግንባር ሲያቀኑ ዘመቻውን እንድቀላቀል በግል እንደጠራሁ ያህል ይሰማኛል፤ እድለኛም ነኝ ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መዝመት ለህዝብ እና ለሰራዊታችን ያላቸውን ክብር እና ሀገር ወዳድነትን የሚያመለክት እና ዘመቻው በእሳቸው መመራቱ ለእኛ ትልቅ እድል ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በኢትዮ- ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ያደረግነውን ጦርነት ዛሬም ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመደገፍ እኔ እና ጓደኞቼ ለመድገም እና ጠላትን ድባቅ ለመምታት እና ታግለን ለማታገል ዝግጁ ነን ብለዋል።
አንድ መሪ ወደ ጦር ሜዳ መሄዱ ለእኛ ትልቅ እድል እና ለወጣቱ ደግሞ ትምህርት ነው፤ወጣቱ ይህን አርአያ ተከትለው የውስጥ እና የውጭ ጠላቶቻችንን አንድ ሆኖ ማንበርከክ እንዳለበት ነው የተናገሩት።
ሰራዊቱ ስንቅ እና የኋላ ደጀን ያስፈልገዋል ያሉት አስር አለቃ መኮንን፤ ህብረተሰቡ አካባቢውን በመጠበቅና ስንቅ በማዘጋጀት ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አመልክተዋል።
ከዚህ ባለፈ በተለይ ወጣቱ የጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድን አርአያነት በመከተል ሀገሩን ማዳን ይጠበቅበታል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፤ከእንግዲህ መከላከያን በግንባር ሆነው ለመምራት መዝመታቸውንና ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ ብለው በወቅቱ መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።