የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት እውነተኛ መሪ ሁል ጊዜ ከፊት የሚሰለፍ መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት እውነተኛ መሪ ሁል ጊዜ ከፊት የሚሰለፍ መሆኑን በተግባር ያሳየ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመት እውነተኛ መሪ ሁል ጊዜ ከፊት መሰለፉን ያሳየ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፤ በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ትኩረት በማድረግ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ "ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ፤ ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሱ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ!" ማለታቸውን ጠቅሰዋል።
በዚሁ መሰረት ከትናንት ማለዳ ጀምረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር በመገኘት ሰራዊቱን በመምራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባር እውነተኛ መሪ ሁል ጊዜ ከፊት የሚሰለፍ መሆኑን በተግባር ያሳየ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የአርዓያነት እሴት የመነጨ የታላቅ መሪነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት ቃል በተግባር ለመሆኑ ማሳያ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የቀደምት ኢትዮጵያ አባቶችን አርዓያ የተከተለ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
"ከኢትዮጵያ በላይ ምንም ነገር የለም" ያሉት ዶክተር ለገሰ፤ ሁሉም ነገር ያለ አገር የማይቻል በመሆኑ ሁላችንም ለአገራችን ህልውና በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
ኢትዮጵያ የመላ ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት በመሆኗ ይህንኑ ታሪክ ለማስቀጠል መዘጋጀት አለብን ነው ያሉት።
ኢትዮጵያዊያን የአገር ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ መሪያቸውን በመከተል መዝመት እንዳለባቸው ገልጸው ሁሉም በየተሰማራበት የሙያ መስክ አገርና ህዝብን ለማገልገል ሊዘጋጅ ይገባል ነው ያሉት።
የተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙሃን "በነጭ ውሸታቸው" መቀጠላቸወን ገልጸው፤ አንዳንድ ኤምባሲዎችም የሚያወጡት መግለጫ የኢትዮጵያን ትክክለኛ አሁናዊ ሁኔታ የሚገልጽ አይደለም ብለዋል፡፡
ኤምባሲዎቹ ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ቢያወጡም ዜጎቻቸው ሰላም መሆኑን በመረዳት ስራቸውን ተረጋግተው በማከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዕዝ በቅንጅት በሰራው ውጤታማ ተግባርም በአዲስ አበባ እና ዙሪያ ታቅዶ የነበረን የሸብር ተግባር በማክሸፍ በርካታ ግለሰቦች ከነ ኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ዶክተር ለገሰ ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው በመዝመት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው የሚቀሩ አመራሮችም መደበኛ ሥራቸው ላይ ትኩረት አድርገው ይሰራሉ ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ይህንን የሚያስተባብሩ መሆኑም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡