የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት የህልውና ዘመቻውን ለማሳካት ወሳኝነት አለው - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት የህልውና ዘመቻውን ለማሳካት ወሳኝነት አለው
ድሬዳዋ ፤ ህዳር 15/2014(ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት የተጀመረውን የነጻነት ትግል ለማሳካትና የውሸት ፕሮፓጋንዳ ለማክሸፍ ወሳኝነት አለው ይላሉ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን።
ምሁራኑ ጦር ሜዳ ዘምተው ለእናት ሀገራቸው ህይወታቸውን ለመስጠት ተዘጋጅተዋል፡፡
የአመራሩ ጦርነት ሜዳ መዋል በምዕራባዊያን ሚዲያዎችና ተላላኪዎቻቸው ሀገር ለማፍረስ የሚካሄዱትን ፕሮፓጋንዳ ለማምከንና ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን የህልውና ጦርነት ለአለም እንደሚያስገነዝብ ነው ምሁራኑ ያስረዱት፡፡
ሱራፌል ጌታሁን በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሣይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና የፖለቲካ ተንታኝ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመታቸው በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያፋጥንና የሚያረጋግጥ ይሆናል ሲሉ ምሁሩ ያብራራሉ።
በሠራዊቱና በየደረጃው በሚገኘው ዜጎች ውስጥ ከፍተኛ የሞራልና የተነሳሽነት ስሜትም ይፈጥራል፡፡
በጦርነት ሂደት ውስጥ ሊፈጠር የሚችልን ውጣ ውረድ የበዛባቸው የቢሮክራሲ ሰንሰለቶች አልባት በመስጠት የእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ጦርነቱንና የጥፋት ተላላኪዎችን በህግ ለመጠየቅ ያግዛልም ብለዋል።
እንደ ምሁሩ ገለጻ፤ የመሪዎቹ ቁርጠኝነትና ሀገር ወዳድነት በመላው አለም የተጀመረው “ የይበቃል ዘመቻ” በማቀጣጠልና የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች በመላው አለም የጀመሩትን ህዝባዊ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ያጠናክራል፡፡
ይበልጥኑ የፓን አፍሪካኒዝም ዳግም ውልደትና ዳግም በመላው አለም ጥቁር ህዝቦች ዘንድ እንዲቀጣጠልም ያነቃቃል፡፡
በላቲን አሜሪካ ፣ ካሪቢያን፣ አፍሪካ፣ አውሮፓና አሜሪካ አደባባዮች የተካሄዱት የነጻነት ሰልፎች የፓን አፍሪካኒዝም ምልክትና አፍሪካን ለማፍረስ የሚደረገውን የኒዎ ኮሎኒያሊዝም ሴራ ለማክሸፍ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ነው ምሁሩ ያስረዱት።
በምዕራባዊያን ዘንድ ድንጋጤ የፈጠሩት ህዝባዊ ሰልፎች አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የምትከተለው የተሣሣተ ፖሊሲ ዳግም እንድትፈትሽ ያደርጋታል በማለት የሰልፉን አንደምታ ተንትነዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጦር ሜዳ መሰለፋቸው በአለም አደባባይ የተጀመረውን ንቅናቄ እንዲጠናከር፣ የኢትዮጵያ የህልውና ተጋድሎ እንዲታወቅና የዲፒሎማሲ የበላይነት እንድናገኝ መሠረታዊ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ኤምባሲዎቻችን ኢትዮጵያ የያዘችውን ታላቅ አፍሪካዊ እውነት ለአለም በማሳወቅና በማስረዳት የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት ይበልጥ መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡
ከሌሎች ምሁራን ጋር በመተባበር ባለን እውቀት ፈጣን መፍትሄ አመላካች ጥናቶችን በማድረግ ሀገርን ለማሻገርና ከተጋረጠብን የእጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት እንረባረባለን ብለዋል፡፡
"እኔ ገንዘቤን፣ እውቀቴን ብቻ ሣይሆን ህይወቴን ለመስጠት ግንባር ዘምቼ ኃላፊነቴን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ " ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መግባት የምዕራባዊያን ብሎም የነሱ አፈቀላጤ የሆኑትን ሚዲያዎች ፕሮፓጋንዳ ከምንጩ ለመድፈንና ኢትዮጵያ ለህልውናዋ የምታካሂደውን ጦርነት ትክክለኛነት ለአለም ለማሳወቅ ያስችላል ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ፅሁፍና የፎክለር ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ነጋ አበራ ናቸው።
አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባዊያን በእጅ አዙር የከፈቱብን ጦርነት የአፍሪካዊያንን የነፃነት ትግል ዳግም እንዲፀነስ መንገድ እየከፈተ ነው፡፡
እንደ ዶክተር ነጋ ገለፃ ፤ የመሪው መዝመት ህዝባዊ ማዕበልን የሚፈጥርና ለህልውና መረጋገጥ እያካሄድን የሚገኘውን ጦርነት ከግብ ለማድረስ ያግዛል፡፡
ይህም ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ዕውንነት ማረጋገጥ መቻል ነው፤ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ “የውሃ ኒውክለር” በመታጠቅ በአፍሪካ ቀንድና በምስራቅ አፍሪካ የነበራትን ታሪካዊ ቦታና ተሰሚነቷን እንድታረጋግጥ አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ነው ምሁሩ ያብራሩት፡፡
በየደረጃው የሚገኘው ህብረተሰብ ይህን የህልውና ዘመቻ እንዲሳካና ኢትዮጵያችን ከፍ ብላ እንድታብብ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ የአሸባሪው ተላላኪዎች ማጽዳት ላይ ሣይዘናጋ በትጋት መረባረብ እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡
የመሪው ግንባር መዝመት ሀገርን ለማዳን ያግዛል፤ ህዝባዊ ማዕበሉን ይበልጥ ለማቀጣጠልም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ነው ያሉት ዶክተር ነጋ፡፡
ዶክተር ነጋ በሙያቸው ለሀገራቸው ህልውና መረጋገጥ ያለመታከት ከሚያደርጉት ድጋፍ ባሻገር ግንባር በመሰለፍ የዜግነት ግዴታቸውን በመወጣት የተሻለች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር የድርሻቸውን ለመወጣት ተዘጋጀተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምዕራባዊያንና ተላላኪው አሸባሪው የህወሃት ቡድን የደቀኑባትን አደጋ ለመቀልበስ ጠቅላይ ሚኒስትር ከፊት መሰለፋቸው ለሁሉም አመራር ወሳኝና መሠረታዊ ትርጉም አለው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲውየምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር ሰለሞን ዘሪሁን ናቸው፡፡
ዛሬ የገጠመን የህልውና ፈተና በጠንካራ ህዝባዊ ትስስር የበለፀገች ሀገር ለመገንባት በየደረጃው ያለው አመራር ከመቼውም ጊዜ በላይ ግንባር ቀደም ሆኖ በመትጋት አለበት ብለዋል፡፡
ለችግሩ መፍትሄው አንድም በግንባር ጦርነት ከፊት በመሆን በሌላ በኩል ደግሞ ግንባር የተጓዘውን አርአያነት በመከተል የሚመራውን ተቋም የልማትና የብልጽግና ውጥኖች በቁርጠኝነት በማስፈጸምና በመፈጸም ይሆናል ብለዋል ምሁሩ፡፡
ዘንድሮ የተሻለ ልማትና መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ ደረጃቸውን የጠበቁ ችግር ፈቺ ምርምሮች እውን እንዲሆኑ እኔ አርአያ ሆኜ በቁርጠኝነት ተቋሜን እመራለሁ ብለዋል፡፡