ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሰራዊት 82 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሰራዊት 82 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሰራዊት 82 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ ተደረገ።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ፤ የአሸባሪውን ህወሃት አገር የማፍረስ እኩይ አላማ ለማክሸፍ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች እየተፋለሙት መሆኑን ገልጸዋል።
በግንባር የተሰለፉትን በመደገፍና በየአካባቢው ሰላምና ፀጥታን በመጠበቅ ረገድ ህዝቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በመሆኑም የአገሩን ነፃነት ለማስከበር እየተዋደቀ ለሚገኘው ሰራዊት ህዝቡ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል ረዲ፤ አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ እያደረገ ያለውን የጥፋት እንቅስቃሴ ለመግታት በሚደረገው የህልውና ዘመቻ ህዝቡ ድጋፍና እገዛውን አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በዚህ ሂደት የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ለመከላከያ ሰራዊት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ጠቅሰው በዛሬው እለትም 82 ሚሊዮን ብር የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ከተደረገው ድጋፍ 32 ሚሊየን ብር በጥሬ ገንዘብ ሲሆን 50 ሚሊዮኑ ደግሞ 250 ሰንጋዎችና 640 በጎችን መሆናቸውን አቶ ጀማል ገልጸዋል።
በክፍለ ከተማ ሰላምና ፀጥታን በመጠበቅ ረገድም ማህበረሰቡ ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር ተደራጅቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የመከላከያ ፋውንዴሽን ምክትል ስራ አስፈፃሚ ኮሎኔል አማን ገለሙ፤ ህዝቡ ለአገር መከላከያ ሰራዊት እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ላደረጉት ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።