ቀጥታ፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር መዝመት ለአፍሪካዊያን ጭምር ትልቅ መልዕክት ያስተላለፈ ነው

እንጅባራ ፤ ህዳር 15/2014(ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሸባሪውን ቡድን የመደምሰስ ትግሉን ለመምራት ወደ ግንባር መዝመታቸው ከኢትዮጵያዊያን አልፎ ለሌሎች አፍሪካዊያን ጭምር ትልቅ መልዕክት ያስተላለፍ ነው ሲሉ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ይናገራሉ። 
ኢዜአ ያነጋገራቸው የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡና በውክልና ለማስተዳደር ለሚፈልጉ ሀገራት ትምህርት ነው።

ፈንታሁን አዳሙ በዩኒቨርሲቲው እያስተማሩ የሚገኙ ዕጩ ዶክተር ሲሆኑ፤ የህልውና ዘመቻው ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ነጻነትን ለማወጅ የሚደረግ ትግል መሆኑን ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ይህንን የሚያጠናክርና ለሌሎች አፍሪካዊያን   የሚያስተላልፈው መልዕክት ትልቅ እንደሆነ ነው የተመለከተው።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች ተላላኪ የሆነው አሸባሪው የህውሃት ቡድንን ሀገር የማፍረስና ህዝብ የማጥፋት እኩይ ሴራውን ማክሸፍ ዳግም የአድዋ ድል መሆኑን አውስተዋል።

"እኛ ኢትዮጵያውያን የሀገር መሪ ግንባር ድረስ ዘምቶ የመከላከያ ሰራዊቱንና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎችን ሲያደራጅ ቀደም በመሰለፍ ድል ከማድረግ የሚያግደን ሃይል የለም" ብለዋል።

 መላ አፍሪካውያንም ለውክልና ጦርነት የተነሳሱ አሜሪካ ጨምሮ የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሴራ ለማክሸፍ ከሀገራችንና መሪያችን ጎን በመሰለፍ ለነጻነታቸው ድምጻቸውን ማሰማት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ሌላኛው የዩኒቨርሲቲው መምህርት የኔወርቅ አለምነህ፤  ጦርነቱ በምዕራባውያን ድጋፍና ተሳትፎ እየተመራ የሚካሄድ ውሰብስብና አስቸጋሪ ቢሆንም በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ ከታሪክ መረዳት ተገቢ መሆኑን ነው ያወሱት።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር መዝመት ለሌሎች አፍሪካዊያን   የሚያስተላልፈው መልዕክት ትልቅ ከመሆኑም ባለፈ መላ ኢትዮጵያዊያን  በማነቃነቅና የሰራዊቱን ሞራል በመገንባት አኩሪ ድል ለማስመዝገብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

"በጦር ግንባር ተገኝቼ ጦር እመራለሁ፤ ህዝቡ ይከተለኝ" ማለታቸው አሸባሪውን ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመደምሰስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ  እንደሆነ  አስረድተዋል።

በዚህ ወቅት የመሪያችን ቃል ተቀብለን መሳተፍ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ  ጥሪውን ተቀብሎ በሚችለው ሁሉ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ነው አስተያየታቸውን የሰጡት።

"መዝመት የነጻነት ወይ የሞት ጉዳይ ነው፤  እኛ ኢትዮጵያዊያን የአሸባሪውን ቡድን ለመደምሰስ እስከ መጨረሻው ድረስ እንዋጋለን " ያሉት ደግሞ ሌላዋ የዩኒቨርሲቲው መምህርት ደመቁ አካሉ ናቸው።

የጠቅላይ ሚኒስትራችን ለዳግም አድዋ ቆርጠው መነሳታቸው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡና በውክልና ለማስተዳደር ለሚፈልጉ ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

 ይህ ትግል የመላ ጥቁር ሕዝቦች ነው፤ ኢትዮጵያን አንበርክኮ ጥቁር ሕዝብን ለማሳፈርና አዲሱን የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጫን የሚደረግ ሤራ በመሆኑ  በፓን አፍሪካኒዝም  መንፈስ ሁላችሁም ጥቁር ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቆሙ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ካስተላለፉት መልዕክት መካከል ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም