እናት ሀገር ኢትዮጵያ ስትጣራ በዝምታ ማለፍ አንችልም--የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
እናት ሀገር ኢትዮጵያ ስትጣራ በዝምታ ማለፍ አንችልም--የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች
ዲላ (ኢዜአ) ህዳር 14/2014 እናት ሀገር ኢትዮጵያ ስትጣራ በዝምታ ማለፍ አንደማይችሉ የጌዴኦ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች እንዳሉት እናት ሀገር ኢትዮጵያ ስትጣራ በዝምታ ማለፍ አይችሉም።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ አርዓያን ተከትለን በአሸባሪው ህወሓት የተጋረጠብንን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ ጠላትን በግንባር እንፋለማለን ብለዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል በዲላ ከተማ የመንግስት ሠራተኛው አቶ አብርሃም መኩሪያ የጠቅላይ ሚኒስትራችን በግንባር መዝመት ለሀገራቸው ክብርና ነጻነት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ማዳን የመንግስት ጉዳይ ብቻ እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ሀገር ፈተና ውስጥ ገብታ ስትጣራ በርቀት ማየት የእኛ የኢትዮጵያዊያን ባህል አይደለም ብለዋል።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን አርዓያ ተከትለው ሀገርና ህዝብ የተጋረጠባቸውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በሚያስፈልገው ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
"የተከፈተብን ጦርነት ከአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና ለእኛ አሻንጉሊት መንግስት መመስረት ከሚፈልጉ ምዕራባዊያን ጭምር ነው" ያሉት አቶ አብርሃም፣ የሀገርን ክብር ለማስጠበቅ እንደ ህዝብ አንድነትን ማጽናት እንደሚያስፈለግ ገልጸዋል።
"ኢትዮጵያ ለቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት በመሆኗ ጥቁር አፍሪካዊያንም ከኢትዮጵያዊያን ጋር በአንድነት ሊነሱ ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።
"እናት ሀገር ኢትዮጵያ ስትጠራን መቅረት አንችልም" የሚሉት ደግሞ የቀድሞ የጦር ሠራዊት አባል ወታደር ፈጠነ ጎበና ናቸው።
"ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ አትገነጠልም ብለን ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ስንዋጋ የወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም በግንባር ተገኙ ከተባለ የወታደሮች ወኔና ለውጊያ ያለን ተነሳሽነት በእጅጉ ያይል ነበር" ሲሉ አስታውሰዋል።
ወታደር ፈጠነ እንዳሉት፣ ዛሬ ጠቅላይ ሚንስትራችን ሀገር ለማፍረስ የተነሳውን ጠላት በግንባር ለመፋለም መዝመታቸው ለሠራዊቱ ከፍተኛ ተነሳሽነት ከመፍጠሩ ባለፈ ትውልድ የሚያሻገር ታሪክ ማስቀመጥ ነው ብለዋል።
"የአባቶቻችንን የነጻነት ታሪክ እኛ ልናበላሽ አይገባም" ያሉት ወታደር ፈጠነ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቁርጠኝነት በመነሳት ለእናት ሀገራቸው ዳግም ዘብ ለመቆም መወሰናቸውን ገልጸዋል።
ወጣት ሳልሳዊት ገብረወልድ በበኩሏ አሸባሪው ህውሓት እየፈጸመ ያለውን ዘግናኝ ድርጊትና ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ለማስቆም ቡድኑን ማጥፋት እንደሚገባ ጠቁማ፣ ለዚህም በሚያስፈልገው ሁሉ የድርሻዋን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች።
"ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን መላው የአፍሪካ ህዝቦች ነፃነታችንን የምናረጋግጥበት ወሳኝ ወቅት በመሆኑ ፈተናውን በድል ለመሻጋር በጋራ እንቁም" ብላለች
እንደ ወጣቷ ገለጻ የጠቅላይ ሚንስትራችን በግንባር የመዝመት ውሳኔ ጥንካሪያቸውንና ለሀገራችው ያላቸውን ፍቅር በተግባር የሚያሳይ ነው።
ወጣቱች የሀገር ፍቅርን ከእሳቸው እንዲማሩ ባማድረግ በኩልም ውሳኔያቸው የራሱ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ወጣቷ የገለጸችው።
"የዶክተር ዐቢይ የመዝመት ውሳኔ በእኔና በሌሎችም ኢትዮጵያዊያን ላይ ትልቅ መነሳሳት ፈጥሯል፤ በምችለው ሁሉ ከጎናቸው ለመቆም ቆርጬ ተነስቺያለሁ" ብላለች።