የሕልውና ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማሸነፍ በሁሉም ግንባር በፅናትና በቆራጥነት መታገል ይገባል---ዶክተር ይልቃል ከፍአለ - ኢዜአ አማርኛ
የሕልውና ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማሸነፍ በሁሉም ግንባር በፅናትና በቆራጥነት መታገል ይገባል---ዶክተር ይልቃል ከፍአለ
ባህር ዳር ህዳር 14/2014 /ኢዜአ/ አሸባሪው ህወሓት በሀገራችን ላይ የከፈተውን የሕልውና ጦርነት በአጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ በሁሉም ግንባር የሽብር ቡድኑን በፅናትና በቆራጥነት መታገል እንደሚገባ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፍአለ ገለፁ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የክተት ጥሪውን ተቀብለው ለመዝመት ከተዘጋጁ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር በባህር ዳር ከተማ መክረዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በእዚህ ወቅት እንዳሉት ህልውናችን እስኪረጋገጥ ድረስ ኢትዮጵያን ማፍረስ ግብ አድርጎ የተነሳውን የሽብር ቡድን ለመደምሰስ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
"አሸናፊነታችን የሚረጋገጠው የሽብር ቡድኑን አጥፊነትና ሀገር አፍራሽነት ተረድተን በቆራጥነት ስንታገለውና በያለበት ስንደመስሰው ነው ሲሉም" አክለዋል።
ጦርነቱ የዜጎችን ሰቆቃና በደል ለማስቆም፣ ሀገርን ከብተና ለመታደግና ለነፃነት ሲባል የሚደረግ ፍትሃዊ ጦርነት መሆኑንም ተናግረዋል።
"ያለመስዋትነት ዘላቂ ነፃነት አይገኝም'' ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ለዚህም ሁሉም አሸባሪውን ህወሓት በቆራጥነት መፋለምና መደምሰስ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
''ይህን ጦርነት ማሸነፋችን አይቀርም፤ አትጠራጠሩ'' ያሉት ዶክተር ይልቃል፣ "ማሸነፋችን ደግሞ በእኛ ትግል፣ ፅናት፣ መስዋዕትነትና አንድነት የተወሰነ ነው" ሲሉም ገልጸዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍሰሃ ደስአለኝ በበኩላቸው፣ ጊዜው ጠላት ኃይሉን አሰባስቦ ወረራና ዝርፊያ የፈፀመበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው ህወሓት በየደረሰበት ንጹሀንን ከመግደል ባለፈ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውጭና ከውስጥ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ወግኖ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል እየፈፀመ መሆኑንም ገልጸዋል።
የአሸባሪውን ዕድሜ ለማሳጠር ህዝቡ፣ ባለሃብቱ፣ ወጣቱ፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት፣ ዲያስፖራው የሚችልውን ሁሉ እያደረገ ለሕልውና ዘመቻው ስኬታማነት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም አቶ ፍሰሀ ተናግረዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በግንባር ተሰልፈው ጦርነቱን ለመምራት ያሳዩት ቁርጠኝነት ሠራዊቱ የበለጠ ለድል እንዲነቃቃ፣ በየአካባቢው የሚዘምተውም እንዲበረታታ ያደርጋል" ብለዋል።
አሸባሪውን ህወሓት ፈጥኖ ለመደምሰስ መላው ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ኃላፊው አሳስበዋል።
በመድረኩ ከተሳተፉ የክልሉ የመንግስት ሠራተኞ መካከል ወይዘሮ ማስተዋል አለባቸው በበኩላቸው የሽብር ቡድኑን ወረራና ጥቃት ፈጥኖ መመከት ካልተቻለ ዳፋው በእያንዳንዱ ላይ መድረሱ አይቀርም።
''በወንድሞቼ፣ በእህቶቼ፣ በእናቶቼ እና በአባቶቼ ላይ የደረሰው ግፍና በደል ዳግም በእኔ ላይ እንዳይፈጸም በግንባር ተሰልፌ አሸባሪውን ለመፋለም ወስኛለሁ'' ብለዋል።
"ከዚህ ጭራቅ ከሆነ የሽብር በድን ጋር በደንብ እንተዋወቃለን'' ያሉት ደግሞ ሌላው ሠራተኛ መቶ አለቃ አበበ ተመስገን ናቸው።
"እኛ የጥንት ጀግኖች አባቶች ልጆች ነን" ያሉት ዘማቹ፣ በግንባር አሸባሪውን በመደምሰስ ድል ለማስመዝገብ ቆርጠው መነሳታቸውን ተናግረዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚሳተፉበት ሀገርን የማዳን የህልውና ዘመቻ ላይ መሳተፌ እድለኛ ነኝ፤ ሃገሬ ነፃ ሳትወጣ ከግንባር ወደቤቴ አልመለስም" ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የመንግስት ሠራተኞቹ ሀገርና ህዝብ አሁን የገጠማቸውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርዓያነት ተከትለው ወደግንባር በመዝመት የሚበቅባቸውን የዜግነት ግደታ ለመወጣት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ በስፋት መክረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።