አሜሪካና አንዳንድ ምእራብ አውሮፓውያን ሃገራት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የሚሰጡት ማስጠንቀቂያ የዲፕሎማሲያዊው ጫና አካል ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሜሪካና አንዳንድ ምእራብ አውሮፓውያን ሃገራት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የሚሰጡት ማስጠንቀቂያ የዲፕሎማሲያዊው ጫና አካል ነው
ህዳር 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሜሪካና የአንዳንድ ምእራብ አውሮፓውያን ሃገራት ዜጎቻቸው ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የሚሰጡት ማስጠንቀቂያ የዲፕሎማሲያዊ ጫና አካል እንደሆነ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ገለጸች፡፡
ሀገራቱ የኢትዮጵያን የህልውና ዘመቻ የተለየ ቅርጽ በመስጠት የኢትዮጵያ መንግስትን ለማስጨነቅና ለመወንጀል ማለማቸውንም አስረድታለች።
የበቃ (#NoMore) ዘመቻ መስራቿ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ ከብላክ ኒውስ ቻናል የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራት ቆይታ እንደገለጸችው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተከታታይ ማስጠንቀቂያዎች በኢትዮጵያውያን ላይ የከፈቱት የስነልቦና ጦርነት አካል ነው።
አሸባሪ ቡድኖቹ ወደ “አዲስ አበባ ተጠግተዋል” በሚል አሜሪካውያንና የሌሎች ሃገራት ዜጎች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የሚደረገው ውትወታ ከእውነታ የራቀ ነው ብላለች፡፡
የፌደራል መንግስት አሸባሪው ህወሃት ይዟቸው የነበሩ ቦታዎችን መልሶ እየተቆጣጠረ ነው ስትልም ገልጻለች።
አሜሪካም ሆነች ምእራባውያን አጋሮቿ ጉዳዩን ማጦዛቸው ለመፍትሄው አያግዝም ያለችው ሄርሜላ፤ የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን ቁሳዊና ሰብአዊ ጉዳት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ ምርመራ ማረጋገጡን ተናግራለች፡፡
ከሃምሌ እስከ መስከረም ድረስ ሰብአዊ እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ ሲላኩ የነበሩ ከ800 በላይ ግዙፍ ተሽከርካሪዎች እንዳልተመለሱ በማስታወስ ለአሸባሪው ድርጅት በሚሰሩ የተመድ ሃላፊዎች ምክንያት ሰብአዊ እርዳታው ጦርነቱን ለማስፋፋት መዋሉን አንስታለች።
የአሸባሪው ድርጅት ተዋጊዎች ወደ አፋርና አማራ ክልሎች ገብተው የፈለጉትን ሲያደርጉና በሺዎች የሚቆጠሩትን ሲገድሉ እንደነበር በራሳቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲያሳዩ መቆየታቸውንም አስረድታለች።
የአሸባሪው ቡድን ዘግናኝ ግድያዎችን እና ከፍተኛ የንብረት ውድመቶችን እያደረሰ መሆኑን የሚያውቁት የአሜሪካ ባለስልጣናት የሽብር ቡድኑን ድርጊት ከማውገዝ ይልቅ ኢትዮጵያ ላይ ተከታታይ ማእቀብ በመጣልና ማስፈራሪያዎችን በመደራረብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ እንዲቆምና ድርድር እንዲጀመር ትእዛዝ መሰል ጥያቄያቸውን ማቅረብ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድታለች።
-አካባቢህን ጠብቅ
_ ወደ ግንባር ዝመት
_ መከላከያን ደግፍ