አሸባሪው ከገባበት መውጫ አጥቶ በያለበት እንዲደመሰስ የተቀናጀ ዘመቻ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ከገባበት መውጫ አጥቶ በያለበት እንዲደመሰስ የተቀናጀ ዘመቻ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ህዳር 15/2014 (ኢዜአ)አሸባሪው ህወሓት ከገባበት መውጫ አጥቶ በያለበት እንዲደመሰስ የተቀናጀ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ ገለጹ።
የጠላት ሃይል ዙሪያውን በእሳት ቀለበት ተከቦ እየተመታ መሆኑን ተገልጿል።
አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ባደረገባቸው አካባቢዎች የሚያደርሰውን ጉዳት ለማስቆምና ቡድኑን ለማጥፋት የጸጥታ ሃይሉ የተቀናጀ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።
በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አለሙ ስሜ፤ የሽብር ቡድኑና ተላላኪዎቹን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ለማጥፋት የተቀናጀ የአመራር ስምሪት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በዚህም ከጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጀምሮ ሁሉም ከፍተኛ አመራሮች ወደ ግንባር መዝመታቸውን ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሓት በወረራ ከገባባቸው አካባቢዎች መውጫ አጥቶ በያለበት እንዲደመሰስ የተቀዳጀ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች የውስጥም የውጭም በመሆናቸው የተደረገው የአመራር ስምሪት ትግሉን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ከፍተኛ አመራሮች ወደ ግንባር የዘመቱት የመከላከያ ሰራዊቱን ስራ ለመተካት ሳይሆን ህዝብን በማስተባበር የሽብር ቡድኑ በየትኛውም አካባቢ መውጪያ እንዳያገኝና ተመልሶ ወደ ተንቤን በርሃ እንዳያመልጥ ለማድረግ መሆኑንም ዶክተር አለሙ ገልጸዋል።
አባቶቻችን የተከበረችና የታፈረች ሀገር እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም መስዋዕትነት ከፍለን ልጆቻችን ቀና ብለው የሚሄዱባት ሀገር ማቆየት አለብን ብለዋል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ጠላትን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት በኢትዮጵያ ላይ የሚመጣን ማንኛውም ጥቃት በብቃት በመመከት ጠላትን አሳፍሮ መመለስ የሚችል አቅም መፈጠሩንም አረጋግጠዋል።
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በበኩላቸው፤ የጠላት ሃይል ዙሪያውን በእሳት ቀለበት ተከቦ እየተመታ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ትግሉን በፍጥነት አጠናቆ ወደ ልማት መመለስ የሚያስችል የተደራጀና ራሱን ለመስዋዕትነት ያዘጋጀ የህዝብ ንቅናቄና አመራር መፈጠሩንም ተናግረዋል።
ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ ግንባር መዝመታቸውን ጠቅሰው ኢትዮጵያን ለማዳን በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።