የምዕራባውያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጩት ዘገባ የጋዜጠኛነት መርህን የጣሰ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የምዕራባውያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጩት ዘገባ የጋዜጠኛነት መርህን የጣሰ ነው
አዲስ አበባ፣ ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያሰራጩት ዘገባ የጋዜጠኛነት መርህን የጣሰ መሆኑን የካናዳ ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር አና ፊዝት-ጌራልድ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የመረጃ ጦርነቱን ለማሸነፍ የተግባቦት እና የዲጂታል ዲፕሎማሲ አቅሙን ማጠናከር እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በተመለከተ ለአንድ ወገን ያደሉ፣ግጭትን የሚያባብሱ እና ኢትዮጵያን የማጠልሸት ግብ ያላቸው ዘገባዎችን እያሰራጩ ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የተቀነባበረና በተደራጀ የመረጃ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
የካናዳ ዊልፍሪድ ላውሪየር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር አና ፊዝት-ጌራልድ የምዕራቡ ዓለም መገናኛ ብዙሃን በኢትዮጵያ ላይ የሚያወጧቸው ዘገባዎች የዚሁ የመረጃ ጦርነት አካል መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙሃኑ የሚያወጧቸው ዘገባዎች ኃላፊነት የጎደላቸው፣የመረጃ ስህተት ያለባቸው እና መሬት ላይ ካለው ነበራዊ እውነት የራቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤንኤን "ሕወሓት አዲስ አበባን ከቧል" ብሎ በሰራው ዘገባ ላይ የተጠቀመው መስሎች ከዚህ ቀደም ትግራይ ውስጥ የተቀረጸ ምስል መሆኑ መረጋገጡን አመልክተዋል።
ይህ የሲኤንኤን ዘገባ የጋዜጠኝነት መርህና ስነ ምግባርን የጣሰ ከመሆኑ ባሻገር ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት መሆኑን ነው ፕሮፌሰር አን የገለጹት።
ሴኤንኤን ከዚህ ቀደም "የመንግስት ኃይሎች በጦርነት የሞቱ ሰዎች አስክሬን በተከዜ ወንዝ ውስጥ ጥሏል" ብሎ የሰራው ዘገባም እንዲሁ ከእውነታ የራቀና የመረጃ ግድፈቶች የነበሩት እንደሆነ ተናግረዋል።
መንግስት ወቅታዊ መረጃዎችን በፍጥነት ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ክፍተት እንደነበረበትና አሁን ላይ አቅሙን እያሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።
አሁን ዓለም ባለችበት የመረጃና የዲጂታል ዘመን በተለይም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰራጩ ዘገባዎች በፍጥነት ተደራሽ እንደሚሆኑ አንስተው፤ በእነዚህ ዘገባዎች የሚፈጥሯቸውን ክፍተት ወዲያው መሙላት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
መንግስት በቅርቡ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ማሳወቁና ይህም ጥሩ የሚባል ጅማሮ መሆኑን ገልጸዋል።
የዲጂታል ዲፕሎማሲ አቅም በማጠናከር ከመደበኛ ዲፕሎማሲ ጋር በማቆራኘት የተሻለ አቅም መፍጠር እንደሚቻል አስረድተዋል።
መንግስት ጠንካራ የተግባቦት አቅም ሊኖረው እንደሚገባ የሚያነሱት ፕሮፌሰር አና፤ ተግባቦቱ አጀንዳ መስጠት የሚችል ፣አዝማሚያዎችን ቀድሞ የሚያይና የሀሳብ ትርክቱ ገዢ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የተግባቦት ባህልን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ውስጥ በስፋት ማስረጽ እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።
መንግስት በዋናነት ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ የፖሊሲ ጉዳዮች አንዱ ስትራቴጂካዊ የተግባቦት ስርዓት መሆኑን ጠቅሰው፤ወጥ የሆነ የመረጃ አሰጣጥ የዲፕሎማሲ ማህበረሰቡን ከኢትዮጵያ ጎን ለማድረግ እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችም በኢትዮጵያ የተግባቦት ባህልን ለማሳደግ የግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም የጥናትና ምርምር ስራዎች ማካሄድ እንዳለባቸው ፕሮፌሰር አና አክለዋል።