ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ዘምተው ተከተሉኝ" ማለታቸው የአደዋ ድል ታሪክ የደገመ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ዘምተው ተከተሉኝ" ማለታቸው የአደዋ ድል ታሪክ የደገመ ነው
ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ "ዘምተው ተከተሉኝ" ማለታቸው የአድዋ ድል ታሪክ የደገመ መሆኑን የቀድሞ ጦር ሰራዊት ከፍተኛ መኮንን ብርጋዴር ጀኔራል ዋሲሁን ንጋቱ ተናገሩ።
በቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ከ30 ዓመታተ በላይ ያገለገሉት ብርጋዴር ጀኔራል ዋሲሁን ንጋቱ፤ አሸባሪው ወያኔ በኢትዮጵያ ሲፈጠር አገር የማፍረስና የባንዳነት ተልእኮ አንገቦ መሆኑን ይናገራሉ።
አሁን ላይ ደግሞ በግልጽ አዋጅ ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ በመነሳት በተግባር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።
የዚህን አሸባሪ ሃይል የረጅም ጊዜ የጥፋት ህልም ለማክሸፍ በሁሉም አውደ ግንባሮች ተሰልፎ መፋለም ይገባል ብለዋል።
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፤ "ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ፤ ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሱ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ!" ብለዋል።
በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ ጥሪ በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የሕልውና አደጋ ለመቀልበስ የሚያስችል የድል አድራጊነት ጥሪ መሆኑን ብርጋዴር ጀኔራል ዋሲሁን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ዘምተው ተከተሉኝ" ማለታቸውም የአድዋ ድል ታሪክ የደገመ መሆኑን አስታውሰዋል።
አሸባሪው የሕወሃት ቡድን ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያዊያን ላይ ያደረሰው ግፍ እና በደል ለመናገር የሚከብድ ዘግናኝ ተግባር መሆኑን ገልጸው በህዝብ ማእበል ተገፍቶ መወገዱን ተናግረዋል።
የሽብር ቡድኑ ከተወገደ በኋላ በኢትዮጵያ ላይ ባወጀው ጦርነት በተለይም በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ ቀጥሏል ነው ያሉት።
በመሆኑም ይህንን ሃይል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ 'አመልህን በጉያህ፤ ስንቅህን በአህያህ' ብለው ካወጁት የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ የአገርን ሉዓላዊነት የማዳን ጥሪ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን ጀኔራል ዋሲሁን ተናግረዋል።
አሁንም የጠቅላይ ሚነስትሩ ወደ ግንባር መሄድ በተፈጥሮው ወታደር ለሆነው ለኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ በግንባር ለሚዋደቀው ሰራዊት ትልቅ ሞራልና መነሳሳትን የሚፈጥር እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መሪዎች ህዝባቸውን አስከትለው በግንባር በመሰለፍ የኢትዮጵያን የግዛት ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ ታሪክ የተለመደ መሆኑንም አንስተዋል።
ዛሬም የ3 ሺህ ዓመታት ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በዚህ ትውልድ መፍረስ ስለማይገባት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጎን በመሰለፍ የኢትዮጵያን ሕልውና መታደግ ይገባል ነው ያሉት።
የሶማሊያ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ወረራ በፈጸመባቸው በ1956 እና 1969 ዓ.ም በምስራቅ ጦርነቶች መሳተፋቸውን ያስታወሱት ብርጋዴር ጀኔራል ዋሲሁን፤ በየጊዜው ኢትዮጵያ ስትደፈር ከታዘቡት የህዝብ ንቅናቄ በበለጠ የወቅቱ ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የውጭ አገራት የሚገኙ የትግራይ ተወላጆችም በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተው አሸባሪውን ሃይል መፋለም አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በየዘመኑ ውስጣዊ ችግር ሲገጥማት ምዕራባዊያን ከችግሯ እንዳትወጣ ሳንካ መሆን ልማዳቸው መሆኑን በሶማሊያ ጦርነት ወቅት የነበረውንም አስታውሰዋል።
አሜሪካ በተለያዩ አገራት ያደረገችው ጣልቃገብነት አገራትን ከማፍርስ ባለፈ ለማንም ጠቅሞ እንደማያውቅ ገልጸው፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ በተቃራኒ አንድ ቡድንን መደገፍ አሳፋሪ እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን ከዚህ በኋላ አምባገነን ስርዓት የሚሸከም ትክሻ እንደሌላቸው፤ ከታሪካዊ ጠላቶች ወግኖ ወደ ስልጣን መመለስ የማይሳካ ቅዥት እንደሆነ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን ጎሰኝነት፣ ጠባብነትን እና የሕወሃትን የመከፋፈል ተልዕኮ ንቀው፤ በአንድነት፣ በመረዳዳት፣ በቅንነት፣ በመተባበር ለአገር ህልውና ሊቆሙ ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ለቀድሞ ሰራዊት አባላት ጥሪ መደረጉን አድንቀው፤ በህልውና ጦርነቱ ያላቸውን ልምድና እውቅት ተጠቅመው ለኢትዮጵያ ህልውን ዘብ እንቆማለን ብለዋል።
ጉዳዩ አጣዳፊ በመሆኑ የዘመናችን አረመኔ ምሳሌ የሆነውን የሕወሃት ጀሌዎችንና ሽፍቶችን በመደምሰስ በአጭር ጊዜ ወደ ልማት መመለስ ይገባል ብለዋል።
ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ በጠላት ስትወረር ክፍያ የፈጸመችባቸው የጦር መሳሪያዎች ሳይቀር በምዕራብ አገራት እንደተከለከለች አስታውሰው፤ ዳሩ በክፉ ቀን ኩባን መሰል ወዳጅ አገራትም ከጎኗ መቆማቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የምዕራባዊያንን ጫና ለመቋቋም ከአፍሪካ አገራት ጋር ያለውን ፓን አፍሪካዊነት ማጎልበት እና ከሌሎች ወዳጅ አገሮች ጋር ግንኙነትን በማጠናከር ተዕጽኖውን መቋቋም ይገባል ብለዋል።