ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር ወደ ግንባር ለመዝመት ያሳለፉት ውሳኔ ህብረተሰቡን የሚያነሳሳ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር ወደ ግንባር ለመዝመት ያሳለፉት ውሳኔ ህብረተሰቡን የሚያነሳሳ ነው
ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር ወደ ግንባር ለመዝመት ያሳለፉት ውሳኔ ህብረተሰቡን የሚያነሳሳ መሆኑን የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች እና ተቋማት በዛሬው እለት ለመከላከያ ሰራዊት ያሰባሰቡትን ድጋፍ ለከተማ አስተዳደሩ አስረክበዋል፡፡
በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ህልውና ለማስከበር ወደ ግንባር ለመዝመት ያሳለፉት ውሳኔ ህብረተሰቡን የሚያነሳሳ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥራትና ቁጥጥር ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ህይወት ጉጉሳ ኢትዮጵያዊያን አባቶች የተከበረችና ነጻ አገር አስረክበውናል፡፡
ኢትዮጵያ አሸናፊ የምትሆነው በእኛ መስዋዕትነት በመሆኑ የሚጠበቅብንን ኃላፊነት በመወጣት አገራችንን እናሻግራታለን በማለት ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግል ትምህርት ቤቶች አሰሪዎች ማህበር ስራ አስፈፃሚ አባል አሳምነው ደርቤ በበኩላቸው ዜጎች መኖር የሚችሉት አገር በነፃነት ታፍራና ተከብራ ስትኖር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም አገር ለማፍረስ የመጣውን ወራሪ ኃይል ቆሞ የሚመለከት ዜጋ እንደማይኖር አረጋግጠዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት ስልጠና እና ቁጥጥር ባለስልጣን የአራዳ እና የቂርቆስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ፍቅሩ ገቢሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ኃይሎች የተደቀነባትን አደጋ በድል ለመወጣት ትግል ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
ይህን ፈተና ለማለፍ ሁሉም የተግባር ሰው በመሆን ትግሉን መቀላቀል እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባል እና የፌደራል መንግስት ግዢ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢተሳ ደሜ ሁሉም ዜጋ አቅሙ በሚፈቅደው መንገድ አገሩን ማገልገል ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡