ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር በመዝመት አገርን ለማዳን ያሳለፉት ውሳኔ ወቅቱን የጠበቅና በኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳን የሚመዘገብ ነው

13

ህዳር 15/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ግንባር በመዝመት አገርን ለማዳን ያሳለፉት ውሳኔ ወቅቱን የጠበቅና በኢትዮጵያ የታሪክ ድርሳን የሚመዘገብ ነው ሲሉ የኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡

ፓርቲዎቹ ወደ ግንባር በመዝመት የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ነው  የተናገሩት።

ፓርቲዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የአገሪቷ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር አብይ አሕመድ አገር ከተቃጣባት የሕልውና አደጋ ለመታደግ ያሳለፉት ውሳኔ ወቅቱን የጠበቅና ታሪክ የማይረሳው ነው።

የትግራይ ዴሞራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሔ፤ እንደ ፓርቲ አገርን ከሚበታትን  የሕልውና አደጋ ለመታደግ በሚያስፈልገው ሁሉ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንቆማለን ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን እድገት የማይሹ የህወሓት የሽብር ቡድንና ሌሎች ተላላኪዎች በአገር ላይ እያሳደሩ ያለውን ጫና በጋራ መመከት አገራዊ ግዴታ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ፓርቲያቸው አገርን ለማዳን በሚደረገው ማንኛውም ተግባር በጋራ ለመስራትና ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ እስከ ግንባር ድረስ ለመዝመት ቁርጠኛ አቋም ማስቀመጡን በመግለጽ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግንባር በመሰለፍ የህልውና ዘመቻውን ለመምራት መወሰናቸው ለውጥ የሚያመጣ  መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

በህልውናዘመቻው በመሳተፍ ኢትዮጵያን ለማዳን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዩታዊ ፓርቲ /ኢህአፓ /የህዝብ  ግንኙነት  ኃላፊ መጋቤ ብሉይ አብርሃም ናቸው።

''ኢህአፓ ኢትዮጵያን የማዳን ጽኑ አቋም አለው" ብለዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፈለግ በመከተል የህልውና ዘመቻውን በድል ለማጠናቀቅ ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

በኢትዮጵያ አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት ለቋመጡ አካላት ትምህርት መስጠት እንደሚገባ  አመላክተው፤ “በድል ተመልሰን ለዓለማቀፍ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ አሸናፊ መሆኗን እናሳያለን” ብለዋል።

የእናት ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰይፈስላሴ አያሌው፤ ፓርቲያቸው በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የሕልውና አደጋ ለመመከት በሚደረገው ጥረት  ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ሂደት ቀያሪና የአድዋ ድልን ለመድገም እድል ይሰጣል ብለው እንደሚያምኑም ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ “ኢትዮጵያ” የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን! ሲሉ ለመላው ኢትዮጵያውያን ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም