የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆራጥ ውሳኔ ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት ያነሳሳ ነው

83

ጂንካ  ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚንስትሩ ቆራጥ ውሳኔ በሀገር ላይ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት ያነሳሳል ሲሉ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት አቶ ሞኩ አህመድ እንዳሉት ሀገሩ ሲነካ አሜን ብሎ የሚቀበል ኢትዮጵያዊ የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገርን በማስቀደም የህልውና ዘመቻውን በግንባር ለመምራት መዝመታቸው መላውን ኢትዮጵያዊ ያነሳሳ ነው።

"እኛ በገንዘብም በአይነትም በምንችለው ሁሉ ድጋፍ እያደረግን ነው፤ አሁን ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመሰለፈ የሀገር ውስጥና የውጭ ጠላቶችን ለመመከት ተዘጋጅተናል" ብለዋል።

ዋና ሳጅን አያሌው ዘውዴ በበኩላቸው "አሸባሪው ህወሓት ለ27 ዓመታት በባርነት ውስጥ ከቶን ነበር አሁን ደግሞ ለኢትዮጵያ ጠላቶች አሳልፎ ለመስጠት ሀገሩን እየወጋ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

"ጠቅላይ ሚንስትሩ በግንባር መዝመታቸው እውነተኛ ሀገር ወዳድነታቸውን የሚያሳይ፣ የቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎች ታሪክን የተጋሩ የዘመኑ መሪ ያደርጋቸዋል" ሲሉ ገልጸዋል።

ጥንትም በአድዋ ጦርነት ከባርነት ሞት ይሻላል በሚል ጀግኖች አባቶች የውጭ ወራሪን ተዋግተው ድል ማድረጋቸውን ዋና ሳጅን አያሌው ጠቅሰዋል።

አክልውም "አሁንም ባንዳዎችን በመደምሰስ በእጅ አዙር በዘመናዊ ባርነት ኢትዮጵያን ለመግዛት የሚደረገውን ጥረት ማክሸፍ አለብን" ብለዋል።  

ጦርነቱ ከአሸባሪዎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር የሚካሄድ በመሆኑን ስላወቅን ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጎን በመሰለፍ ሀገርን መተዳግ የእኛም ሃላፊነት ነው ሲሉ ገልጸዋል ።

የደቡብ ኦሞ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ እና የብልፅግና ፓርቲ የፓለቲካ ርዕዮተ አለም ሀላፊ አቶ ሎቶሮሲ ካሬ በበኩላቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመዝመት መነሳታቸው ኢትዮጵያውያንን ዳር እስከዳር የሚያነቃንቅ ታሪካዊ ውሳኔ መሆኑን ተናግረዋል።

አመራሩም የእሳቸውን ፈለግ በመከተል ወደ ግንባር እየተመመ መሆኑን ጠቁመው፣ በቅርቡ ወደ ግንባር የሄዱ የዞኑ አመራሮች የእዚሁ ማሳያ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የታወጀብን የውክልና ጦርነት ዳግም በቅኝ ግዛት ለመግዛት ያለመ በመሆኑ ከኢትዮጵያዊያን ባለፈ አፍሪካዊያንም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

እንደ አመራር ለህልውና ዘመቻው የሚጠበቅባቸውን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን ብልፅግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ የፖለቲካና ሪዕዮተ ዓለም ግንባታ ዘርፍ ሀላፊ መቅደስ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ በአድዋ ጦርነት ህዝቡ ከዳር እስከዳር ተነሳስቶ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን ወራሪ ሀይል በጦር በጎራዴ መመከቱን አስታውሰዋል።

"አሁን የታወጀብን ጦርነት ዳግም አድዋ በመሆኑ ከዳር እስከ ዳር በመነሳት በዘመናዊ ባርነት ሊገዛ የመጣውን ወራሪ ሀይልና ተላላኪዎቹን እንመክታል" ብለዋል  

የጠቅላይ ሚንስትሩ በግንባር መዝመት ህዝብን ለድል በማነሳሳት በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።

"ጠቅላይ ሚንስተሩ በዘመናዊ ባርነት አልገዛም፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ተላላኪ መንግስት አይኖርም" በማለት ወራሪ ሀይሉን በግንባር ለመፋለም መነሳታቸው ኢትዮጵያዊነታቸውን ከምንጊዜውም በላይ በተግባር ያረጋግጣል ሲሉም ገልጸዋል

"መሪያችን ጠላትን ለመፋለም በግንባር ተሰልፈው እኛ ቁጭ ብለን አንመለከትም፤ ለመዝመት ዝግጁ ነኝ" ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም