ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ለአፍሪካዊያን ላቀረቡት ጥሪ ፈጣን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ለአፍሪካዊያን ላቀረቡት ጥሪ ፈጣን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል- ምሁራን

ሆሳዕና ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ በመነሳሳት ለአፍሪካዊያን ላቀረቡት ጥሪ ፈጣን ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ የዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አመለከቱ ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግዳጅ ቀጠና መዝመታቸው ዜጎችን ለላቀ ተጋድሎ በማነሳሳት በአጠረ ጊዜ አኩሪ ድል ያጎናጽፋል ይላሉ ምሁራኑ ለኢዜአ በሰጡት አሰተያየት።
አቶ ሳሙኤል ሺበሺ በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ኮሌጅ ኃላፊና መምህር ሲሆኑ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህልውና ዘመቻው ላይ ለመካፈል ወደ ግንባር አውደ ውጊያው መቀላቀላቸው በእጅጉ የሚያኮራ ነው ብለዋል።
ውሳኔው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆራጥና ሀገር ወዳድ መሪ መሆናቸውን በተግባር ያሳየነው ያሉት መምህሩ፤ ይህም የሀገር ህልውናን ለማስከበር ዜጎችን ለላቀ ተጋድሎ በማነሳሳት በአጠረ ግዜ አኩሪ ድል ለማስመዝገብ አቅም እንደሚፈጥር ነው የገለጹት።
እኛ ኢትዮጵያውያን በሀገር ጉዳይ ለሚመጣብን ጠላት የማንበገርና እጅ የማንሰጥ መሆናችንን ለጠላትም ለወዳጅም ግልጽ የሆነ መልዕክት ያስተላልፋል ብለዋል።
በተለይ በኢትዮጵያ ላይ እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ዳፋው ለመላ ጥቁር ህዝቦች የሚተርፍ መሆኑን በውል በመረዳት አፍሪካዊያን በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ በመነሳሳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላቀረቡት ጥሪ ፈጣን ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።
መላው አፍሪካውያን እጅ ለእጅ ተያይዘው በአንድነት በጽናት ከተሰለፉ የሚያጋጥማቸውን ማናቸውንም የምዕራባያዊን ተፅእኖ መቋቋም እንደሚችሉ አስረድተዋል።
በዩኒቨርስቲው የፖለቲካ ሳይንስና ስነ ሰብ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ኤፍሬም አሀዱ በበኩላቸው፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመዝመት ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ከዚህ በፊት ኢትዮጵያን ለመውረር ቋምጠው የመጡ ጠላቶችን በመመከት በአፍረት የተመለሱበትን ገድል የሚያስታውሰን ነው ብለዋል።
ምዕራባውያን ሀገር ለማፍረስ ቀድሞም ቢሆን በቀጥታ እጃቸውን እንደማያስገቡና በተዘዋዋሪ መንገድ ድጋፍ በማድረግ እንደሆነ ያነሱት ረዳት ፕሮፈሰሩ ፤ ይህንን ሴራ ለማምከን የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት ለዜጎች የላቀ መነሳሳትና አንድነት እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
በተለይ የምዕራባውያኑ ቀኝ እጅ በመሆን ሀገር ለማፍረስ እየሰራ የሚገኘውን አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንባር ድረስ በመዝመት መቀላቀላቸው የአንድ ሀገር ወዳድ መሪ መገለጫ ባህሪ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ነፃነቷንና ህልውናዋን አስጠብቃ በመቆየት የምትታወቀውን ኢትዮጵያን በማዳከም ምዕራባውያን በአፍሪካ የበላይነታቸውን አስጠብቀው ለመቆየት የወጠኑት ሴራ እንዳይሳካ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአፍሪካ ሀገራት ላቀረቡት ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ነው ያሉት።
ሁሉም ዜጋ ሀገር የማዳን ጥሪውን በመቀበል ለልጆቻችን ከሚተርፍ ተዘዋዋሪ የቅኝ ግዞት እዳ ለማውጣት መስዋዕትነት ልንከፍል ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንቱ መልዕክታቸው “ኢትዮጵያ” የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን! ” በሚል ካነሷቸው ዋና ዋና ነጥቦች መካከል፡-
ይህ ትግል የመላ ጥቁር ሕዝቦች ትግል ነው፤ ኢትዮጵያ አንበርክኮ ጥቁር ሕዝብን ለማሳፈርና አዲሱን የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጫን የሚደረግ ሤራ ነው፤ለጥቁር ሕዝብ ክብርና ልዕልና ስትሉ፣ በፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ፣ ሁላችሁም ጥቁር ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቆሙ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ ያሉት ይገኙበታል።