የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከተልዕኳቸው ባሻገር ለወገን ደራሽ በመሆን አለኝታነታቸውን በተግባር ማሳየት አለባቸው

46

ህዳር 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከተልዕኳቸው ባሻገር ለወገን ደራሽ በመሆን አለኝታነታቸውን በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው የኢዜአ ሰራተኞች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልገሎት (ኢዜአ) ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደማቸውን ለግሰዋል።

የተቋሙ ሰራተኞች ከዚህ ቀደም የወር ደመወዛቸውን በመለገስ ለሰራዊቱ አጋርነታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን በዛሬው እለት ደግሞ ደማቸውን ለግሰዋል።

በኢዜአ የፌዴራልና አዲስ አበባ ዜናዎች ዳይሬክቶሬት ምክትል ዋና አዘጋጅ የሺመቤት ደመቀ፤ "በተቋሙ በየሶስት ወሩ የደም ልገሳ መርሃ ግብር እየተካሄደ በመሆኑ ለለጋሾች መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል" ብላለች።

በዛሬው እለት በተቋሙ ለአራተኛ ጊዜ ደም መለገሷን ገልፃ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከተልዕኳቸው ባሻገር ለወገን ደራሽ በመሆን አለኝታነታቸውን በተግባር ማሳየት እንዳለባቸው ተናግራለች።

በተቋሙ የዜና ማዕከል ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ወርቅነህ፤ "አገርን ለማዳን ህይወቱን ጭምር እየሰዋ ላለው ሰራዊት ደም መለገስ ብቻ በቂ አይደለም" ብሏል።

የተጀመረው የህልውና ዘመቻ እስኪጠናቀቅ ለሰራዊቱ በተለያየ መልኩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።

በተለይ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን ከተልዕኳቸው ባሻገር በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለህዝብ ያላቸውን እገዛና ድጋፍ ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

የተቋሙ ሰራተኞች አገርን ለማዳን እየተካሄደ ያለውን የህልውና ዘመቻ በተለያየ መልኩ እየደገፉና አጋርነታቸውን እየገለጹ መሆናቸውን ያብራሩት ደግሞ የኢዜአ የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂያዊ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሃንስ ወንዲራድ ናቸው።

"ኢዜአ የህልውና ዘመቻውን በሚመለከት በተለያዩ ግንባሮች ጋዜጠኞችን በማሰማራት ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል" ብለዋል።

የተቋሙ ሰራተኞች ከሙያዊ ሃላፊነታቸው በተጨማሪ ለሰራዊቱ በአይነትና በገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ በየሶስት ወሩ የደም ልገሳ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም