ኢትዮጵያ የመላውን ጥቁር ሕዝብ ትግል እያካሄደች ነው

ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የመላውን ጥቁር ሕዝብ ትግል እያካሄደች መሆኑን የዚምባብዌው ፓን አፍሪካ አቀንቃኝና የታሪክ ባለሙያ ማፖንጋ ጆሹዓ ገለጹ።

ኢትዮጵያን በዘመናት ታሪኳ በምዕራባዊያን ፍላጎትና ጫና ሥር ለማስገባት በርካታ ሴራዎች ቢሸረቡም ሁሉንም ችግሮች ተቋቁማ ማለፍ ችላለች።

በተለይም እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1884 የበርሊን ሥምምነትን ተከትሎ ኢትዮጵያን ለማስገበር የመጣው የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል ያደረገው ወረራ ተጠቃሽ ነው።  

ይሁንና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነት ተመው የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ሕልም በአድዋ ተራሮች ላይ አምክነው የአገሪቷን ነጻነት ማስጠበቅ ችለዋል።

ዳግም ለብቀላ የመጣው ፋሺስት ኢጣሊያ ለሁለተኛ ጊዜ ውርደትን ተከናንቦ የተመለሰ ሲሆን ይህም የኢትዮጵያን አይበገሬነት፤ አልንበረከክም ባይነት ዳግም አስመስክሯል።

ጎን ለጎንም ኢትዮጵያን ለመንካት የመጡ የጎረቤት አገራት ጦር ጭምር ድባቅ በመምታት ኢትዮጵያን መንካት ምን ማለት እንደሆነ ትምህርት ሰጥታ መልሳቸዋለች።

አሁን ደግሞ አንዳንድ የምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የአገሪቷን ሉዓላዊነት እየተጋፉ መሆኑን ምሁራን ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ የራሷን የውስጥ ጉዳይ በራሷ ውሳኔ እንዳትሰጥ ማዕቀብ ጭምር በመጣል እጅ እየጠመዘዙና የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን የመጣውንና በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራውን ሕጋዊ መንግሥት የማጠልሸት ሥራ ውስጥ መግባታቸውንም እንዲሁ።

ለዚህም በምዕራባዊያኑ አገራት የሚዘወሩት ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በትሮይ ፈረስነት የኢትዮጵያን መንግሥት ቅቡልነት ለመሸርሸር በቀዳሚነት መሰለፋቸውንም ጠቁመዋል።

የዚምባብዌው ፓን አፍሪካኒስት አቀንቃኝ ማፖንጋ ጆሹዓ እንደተናገሩት፤ የምዕራባዊያኑ ዓለም አሁን ላይ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፍተዋል ብለዋል።

ጦርነቱን ከኢትዮጵያ ጋር ሳይሆን ከመላው አፍሪካ ጋር መሆኑንም ነው ያነሱት።

በመሆኑም አፍሪካዊያን በአንድነት በመቆም በተለይም አፍሪካ ኅብረት በምዕራቡ ዓለም የሚካሄደውን የተቀነባበረ ሴራ መከላከል እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በተለይም አንድ የአፍሪካ አገር መንካት ማለት ሙሉ አፍሪካ አገር መንካት መሆኑን መላው የአህጉሪቱ ሕዝብ ሊያውቀውና ሊገነዘበው እንደሚገባ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።  

ምዕራባዊያኑ በኢትዮጵያ የመንግሥት ግልበጣ ማድረግ እንደሚፈልጉ ገልጸው፤ ይህ አይነቱ ሴራቸው ነገ ከነገ ወዲያ በሌሎች የአፍሪካ አገራት ላይ ሊቃጣ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ስለዚህም አፍሪካዊያን ይህንን አዲሱን የቅኝ ግዛት ሥርዓት በጋራ መቃወም እንዳለባቸው ነው የፓን አፍሪካ አቀንቃኙ ማፖንጋ ጆሹዓ የሚናገሩት።     

ዴንማርካዊው የፖለቲካ ምሁር ፕሮፌሰር ቶቢያስ ሃግማን በበኩላቸው ምዕራባዊያን በሚዘውሯቸው ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን እውነታ በተሳሳተ መልኩ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።  

በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራውንና ከፍተኛ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለውን መንግሥት ለማንኳሰስ የማጠልሸት ሥራ እየሰሩ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ነጻ አገር ሆና የቆየች መሆኗን አንስተው በአገሪቷ ያለውን ችግር በሯሷ አቅም መፍታት የምትችለው በመሆኑ ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልገው ተናግረዋል።

እነዚህም አገራት ከዚህ አፍራሽ አካሄዳቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም "ትግሉ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ትግል ነው" ኢትዮጵያን አንበርክኮ ጥቁር ሕዝብን ለማሳፈርና አዲሱን የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጫን የሚደረግ ሤራ ነው" ብለዋል።

መላው የጥቁር ሕዝብም ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆም "ለጥቁር ሕዝብ ክብርና ልዕልና ስትሉ፣ በፓን አፍሪካ መንፈስ፣ ሁላችሁም ጥቁር ሕዝቦች፣ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቆሙ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ" ነው ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥሪ መላውን የጥቁር ሕዝብ እንደሚያነሳሳና ትግሉ አህጉራዊ ይዘት እንደሚኖረው የተናገሩት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው።

ይህም አፍሪካዊያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ለመከላከል እንደሚያስችላቸው ጠቁመው ይህንን የምዕራቡ ዓለም ጫና ለማቃለል የሚያስችሉ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም