መሪው ሲዘምት ህዝብ ዝም ብሎ አይመለከትም

20

ደብረ ብርሃን ፤ መተማ ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) ሀገርን ከወራሪ ጠላት ነጻ ለማውጣት መሪው ሲዘምት ህዝብ ዝም ብሎ አይመለከትም ይላሉ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት አባል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች ኢዜአ ያነጋገራቸው  የቀድሞው  ሰራዊት አባላት  የጠቅላይ ሚኒስትር ሀገራዊ ጥሪ ተከትለው በግንባር በመሰለፍ ሀገርን ለማዳን እንደሚዘምቱ ነው የሚገልጹት።

መቶ አለቃ ሰለሞን ዘለቀ የሰሜን ሸዋ ዞን   የቀድሞ ሰራዊት አባላት የልማትና የድጋፍ ማህበር ሰብሰቢ ናቸው።

አንድ የሀገር መሪ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ተስፋ ለማሸጋገር በጦር ሜዳ በግንባር ቀደምትነት መዝመታቸው ለትውልዱ ኩራት ነው ብለዋል መቶ አለቃ ሰለሞን በሰጡት አስተያየት።

ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን እንደዚህ ያሉ መሪ ሲወጣና  ሀገርን ከወራሪ ጠላት ነጻ ለማውጣት  ሲዘምት ህዝብ ዝም ብሎ አይመለከትም ያሉት አስተያየት ሰጪው ፤ ለዚህም እሳቸው  እድሜያቸው ሳይገድባቸው ለመዝመት መዘጋጀታቸውን ነው የገለጹት።

''ወታደር የሚመስለው መሪውን ነው'' ያሉት መቶ አለቃ ሰለሞን፤  ጦርነቱ ህዝባዊ በመሆኑ መለዮ ለባሹም ይሁን መለዮ ለባሽ ያልሆነው ህዝብን ያነቃቃ ውሳኔ  ነው ብለዋል።

የህልውና ዘመቻው በሀገር አፍራሽና ሀገር በሚገነባ ሀይል መካከል በመሆኑ ሀገር እንዳይፈርስ ሁሉም አቅሙ በፈቀደ መልኩ ሊደግፍ እንደሚገባም አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚስትሩ ለመዝመት መወሰናቸው ሀገርን ከጠላት ወረራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጽዳት ያስችላል ያሉት ደግሞ በቀድሞ በኢትዮጵያ ባህር ሀይል ማሪን ኩማንዶ አሰልጣኝ የነበሩት ፒቲ ኦፊሰር ገረመው ግርማየ ናቸው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት ለሀገራችን መስዋእትነት ለመክፈል የነበረንን ጥያቄም የመለሰ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የክተት ጥሪ ተቀብለን እሳቸውን በመከተል በግንባር ለመሰለፍ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውኃ ከተማ ከሚኖሩ የቀድሞ የሰራዊት አባላት መካከል ወታደር አዱኛ አበበ እንደተናገሩት፤  የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላትን አሳፍሮ መመለስና መደምሰስ መገለጫው  ነው።

 ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ተሰልፈው  ያላቸውን ልምድና እውቀት ተጠቅመው የእናት ጡት ነካሾችን ለመደምሰስ  ዝግጁ  እንደሆኑ ነው ያስታወቁት።

ሌላኛው የዚሁ ከተማ ነዋሪ ወታደር ባይተኩስ ኪዳኑ በበኩላቸው፤  የሀገር ውስጥ ባንዳዎችን በመደምሰስ የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን በደንብ እንዲያውቋት ማድረግ ይገባል ይላሉ።

''ኢትዮጵያ የማንንም ሉዓላዊ ሀገር ድንበር ጥሳ የማታውቅ፣ በማንም ሀገር ጣልቃ በመግባት የህዝቦቻቸውን ህልውና አደጋ ላይ ጥላ የማታውቅ ናት፤ በዚሁ ልክም በራሷ ሉዓላዊነት ላይ አትደራደርም ብለዋል።

የቀድሞ ሰራዊት አባልና አባት አርበኛ አቶ አሰፋ አድማሴ በበኩላቸው፤  በሀገሩ ጉዳይ ከማይደራደረው ህዝብና የጸጥታ አካል ጎን ሆነው ጠላትን ለመፋለም መነሳሳታቸውን ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህ ውጤታማነት ህዝቡ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም