የአሸንዳ በዓል ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እየሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሸንዳ በዓል ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እየሰራ ነው

መቀሌ ነሃሴ 16/2010 የሴቶች የነፃነትና የዲሞክራሲ መገለጫ የሆነውን የአሸንዳ በዓል ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እየሰራ መሆኑን የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ። በየአመቱ በነሓሴ አጋማሽ በተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የሚገኙ ልጃገረዶች የሚከበረውን የአሸንዳ በዓል ምክንያት በማድረግ ትናንት በመቀሌ ከተማ ''አሸንዳ ለሰላማችንና ለአንድነታችን'' በሚል መሪ ሃሳብ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ሓለፎም እንደገለጹት አሸንዳ ከሶስት ሺህ ዓመታት በፊት ጀምሮ በክልሉ ሲከበር እንደነበረ ገልጸዋል። ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣው ይኸው በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ልጃገረዶች በበዓሉ ላይ ከሚያደርጉት ጨዋታ በተጨማሪ አለባበሳቸውና የሚጠቀሙባቸው ባህላዊ ማስዋቢያዎች ተጠብቀው እንዲሄዱ እየተደረገ ነው። በዓሉ በመካከላቸው ፍቅርና አንድነት እንዲጠናከር የሚያደርግ መሆኑን ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ገልጸዋል። በውይይቱ ላይ በዓሉ የክልሉን ባህል ከማጎልበትና ለቱሪዝም መስህብነት ስለሚኖረው አስተዋፅኦ በተመለከተ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሄዷል፡፡ ምሁራኑ በጽሁፋቸው እንደገለፁት በዓሉ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ቢሆንም ልጃገረዶቹ ከሚለብሱትና ከሚያዜሙት አንፃር ሲታይ ባህላዊ ይዘቱ ያመዝናል። በዓሉን ለቱሪዝም መስህብነት እንዲውል መንግስት የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በውይይት መድረኩ ከተለያዩ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የወጣቶችና ሴቶች ተወካዮችና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ አካላት ተሰታፊ ሆነዋል፡፡ ከተሳታፊዎቹ መካከል የ70 ዓመቷ ወይዘሮ ብርሃን መሓሪ በልጅነት ጊዜያቸው የነበረውን የጨዋታ አይነት፣ ዜማና ግጥም አውስተው በአሁኑ ወቅት በተፈለገው መልኩ እየሄደ ባለመሆኑ ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡