አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና የግብርና ሚኒስቴር ለመከላከያ ሠራዊትና ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ

38

ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ እና የግብርና ሚኒስቴር ለመከላከያ ሠራዊትና ተፈናቃዮች ድጋፍ አደረጉ።

ተቋማቱ ምድር ኃይል በመገኘት ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፤ በመከላከያ ሚኒስቴር የፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሊዊጂ ድጋፉን ተረክበዋል።     

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ፤ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊትም ድጋፍ ያደረገ መሆኑን አስታውሰው በዛሬው እለትም 10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።    

ቀደም ሲል የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ በማስተባበር 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው በቀጣይም ለህልውና ዘመቻው 33 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።  

ለመከላከያ ሠራዊት ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ለተፈናቃዮችም 1 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገበት ሰበአዊ ድጋፍ ማድረጉን ዶክተር ዳምጠው ጠቅሰዋል።  

የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ለመከላከያ ሠራዊት የሞራል ድጋፍና ደም ልገሳ ማድረጉን ጠቅሰው ከ100 በላይ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ወደ ግንባር መዝመታቸውንም ገልጸዋል።  

የግብርና ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማትን በመወከል 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ 20 ሰንጋዎችን ያስረከቡት ደግሞ የሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተሰማ ገብረመድህን ናቸው።

በመከላከያ ሚኒስቴር የፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ፤ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል። 

ኢትዮጵያዊያን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ጥሪ በመቀበል የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከበር በጋራ እንዲቆሙ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም