ቀጥታ፡

የሕልውና ዘመቻውን ከዳር ለማድረስ የተጀመረው የስንቅ ዝግጅት ተጠናክሮ ይቀጥላል

ባህር ዳር ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሀገርን ለመታደግ በግንባር ጠላትን ለመፋለም ያሳለፉትን ውሳኔ ከዳር ለማድረስ የጀመሩትን የስንቅ ዝግጅት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመንግስት ሰራተኞች አስታወቁ።

የአማራ ክልል መሬት አስተዳደር ቢሮ ሰራተኛ ወይዘሮ አዲሴ አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት ምንም ምቹ ሁኔታ ባልነበረበት ሰዓት አያቶቻችን የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ድል ያደረጉት ከዳር እስከ ዳር አንድ ሆነው ተነስተው ነው።

ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር አብሮ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን አሸባሪውን ህወሓ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም በግንባር ለመፋለም ትላንት ያሳለፉት ውሳኔ ሕዝቡ በአንድ እንዲነሳ አድርጓል።

እኔም ደጀን ሆኜ የስንቅ ዝግጅት ከማድረግ ባለፈ ከእሳቸው ጎን ተሰልፌ ጠላትን እንደነ እትጌ ጣይቱ በጦር ሜዳ ተፋልሜ በማሸነፍ የራሴን የታሪክ አሻራ ለማስቀመጥ ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት አሜሪካንን ጨምሮ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገሮች በኢዮጵያ ላይ ያልተገባ ጫና ማሳደር ከጀመሩ ዘመናትን አስቆጥረዋል።

በጠላት የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሳንረበሽ የተጋረጠብንን የሕልውና አደጋ አንድ ሆነን ታግለን በመቀልበስ ጠላትን ድል ልናደርግ ይገባል።     

ሌላኛዋ የመንግስት ሰራተኛ ወይዘሮ የአይንአበባ እንግዳው በበኩላቸው የጀመርነውን የስንቅ ዝግጅት የሕልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስ አጠናክረን እቀጥላለን።

ሀገርን ለማፍረስ የተነሳውን የባንዳዎች ስብስብ ሁላችንም የሕልውና ዘመቻውን በመቀላቀል የተከፈተብንን ጦርነት በአሸናፊነት ልንወጣ ይገባል።

ይህን ሀገር አፍራሽ አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስም ስንቅ ከማዘጋጀት ባለፈ ሁላችንም ጨርቄን፣ ማቄን ሳንል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን ቆመን ጠላትን ለመፋለም ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የአሸባሪውን ህወሓት ሀገር ግብዓተ መሬት ለመፈፀም እኔም በግንባር በመሰለፍ የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅቻለሁ ያሉት ደግሞ ሌላኛው የመንግስት ሰራተኛ አቶ ወርቁ ካሴ ናቸው።

እንዳለፉት መሪዎች ሀገሪቱን ከብተና ለመታደግ ጠቅላይ ሚኒስሩ ያሳለፉት ውሳኔ መልካም በመሆኑ ሁላችንም የእሳቸውን ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ፈለግ ተከትለን ጠላትን ልንፋለም ይገባል።

ለስንዴ እርዳታ ሳንበረከክ ቅጠል በልተንም ሆነ አፈር ልሰን ይህን አሸባሪ ባንዳ በተባበረ ክንድ ደምስሰን ሀገራችንን ነፃ በማውጣት የአያቶቻችንን ታሪክ መድገም ከዚህ ትውልድ ይጠበቃል።

የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ የሎጀስቲክ አስተባባሪ አቶ አወቀ ሲሳይ እንዳሉት የሕልውና ዘመቻውን በድል ለማጠናቀቅ ቢሮው ሰራተኞች የወር ደሞዛቸውን 42 ሚሊዮን ብር ለግሰዋል።

በተጨማሪም ቢሮው በመጀመሪያው ዙር በ17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያዘጋጀውን 100 ኩንታል በሶ፣ 12 ሺህ ካርቶን ብስኩትና እሽግ ውሃ ዛሬ ወደ ግንባር መላኩን ተናግረዋል።

ሀገርን የማዳን ጉዳይ የሁላችንም ድርሻ ነው ያሉት አቶ አወቀ የህልውና ዘመቻው በድል እስኪጠናቀቅ ድረስም የስንቅ ዝግጅቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ግንባር የመዝመት ውሳኔ እኔም ወደ ግንባር ሄጄ ጠላትን ለመፋለም ይበልጥ እንድዘጋጅ አድርጎኛል ሲሉም አስረድተዋል።       

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም