አርቲስት ደመረ ለገሰ የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ ወደ ግንባር ሊዘምት ነው - ኢዜአ አማርኛ
አርቲስት ደመረ ለገሰ የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ ወደ ግንባር ሊዘምት ነው
አዲስ አበባ ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) አርቲስት ደመረ ለገሰ የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ ወደ ግንባር ሊዘምት መሆኑን ገለጸ።
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ "ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ፤ ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሱ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ!" ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልእክት ተከትሎ በርካታ ታዋቂ ሰዎች፣ ፖለቲከኞችና ሌሎችም ግለሰቦች ተከትለዋቸው ለመዝመት ተዘጋጅተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ቆራጥ መሪ እንዳላት በተግባር በማሳየታቸው ሁላችንም ኮርተናል፣ የአገራችንን ህልውና ለማስጠበቅም ተዘጋጅተናል ብሏል።
ከማረሚያ ቤቶች የኦርኬስትራ ቡድን አባላት ጋር ወደ ዘመቻው ለመቀላቀል ተዘጋጅተናል ብሏል።
ኢትዮጵያ በአሸባሪ ቡድን የተደቀነባትን የመፍረስ አደጋ ለመመከት የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት በመሆኑ ለዘመቻው ተዘጋጅተናል ነው ያለው።
ኢትዮጵያ የበርካታ ጀግኖች መገኛ በመሆኗ በአርበኝነት ክብሯንና ሉአላዊነቷን አስጠብቀዋት አስረክበውናል ያለው አርቲሰት ደመረ የአባቶቻችንን አደራ ለማስጠበቅ ተዘጋጅተናል ብሏል።
አርቲስት አያልነህ ሙላቱ በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት የወሰኑት ውሳኔ የቀደሙትን የኢትዮጵያ ጀግና መሪዎች ታሪክ አስታውሶናል ብሏል።
ኢትዮጵያ በጠላት በተወረረችባቸው ጊዜያት መሪዎች ግንባር ቀደም በመሆን ድል ማስመዝገባቸውን ገልጸው እርሳቸውም የአገራቸውን ክብር እንደሚያስጠብቁ አንጠራጠርም ብሏል።
ኢትዮጵያ በዚያድ ባሬ ጊዜ ከሶማሊያ ጋር ባካሄደችው ውጊያ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በጦር ግንባር ተገኝተው ሰራዊቱን በማበረታታት ድል እንዲመዘገብ ማድረጋቸውን አስታውሷል።
ዳግማዊ አጼ ምኒልክም የጣሊያንን ወረራ ለመመከት ወደ አደዋ የተመመውን የኢትዮጵያ ሠራዊት በመምራት ታላቅ ድል ማስመዝገባቸውን ለአብነት ጠቁመዋል።
አሁንም የኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት በህዝቦች የተባበረ ክንድ ይጠበቃል ብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ በመቀበል በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የህልውና ዘመቻ በድል በማጠናቀቅ ለራሳችን ታሪክ የሚጽፍበት ጊዜ አሁን በመሆኑ ሁላችንም ለዘመቻው እንዘጋጅ ብሏል።