"የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔና አገራዊ ጥሪ ለአፍሪካውያን የአሸናፊነት ጥሪ ነው" - ኢዜአ አማርኛ
"የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔና አገራዊ ጥሪ ለአፍሪካውያን የአሸናፊነት ጥሪ ነው"
አዲስ አበባ ህዳር 14/2014(ኢዜአ) "የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔና አገራዊ ጥሪ ለአፍሪካውያን የአሸናፊነት ጥሪ ነው" ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው በውጭ አገራት የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ገለጹ።
የአገር መሪ አገሩን ለማዳን መዝመቱ የአመራር ተምሳሌትነትን የሚሳያይና ሕዝብን የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ "ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ፤ ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለአገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሱ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ!" ብለዋል።
"ኢትዮጵያ" የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓን አፍሪካ መንፈስ ሁሉም ጥቁር ሕዝቦች ከኢትዮጵያ ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል።
በኖርዌይ ኦስሎ የሚኖሩት ወይዘሮ ኢትዮጵያ ዓለምአየሁ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጥሪ የነጻነት፣ የድል አድራጊነት እና የአልሸነፍ ባይነት ጥሪ ነው፤ ለአፍሪካውያንም የአሸናፊነትን ስሜት የሚሰጥ ነው ብለዋል።
"አንድ አገር የሚያስተዳድር መሪ አገርን ለማዳን እዘምታለሁ ብሎ ሲናገር እኛ ማን ነን ቁጭ ብለን የምንጠብቀው አገራችንን ለማዳን መዝመት አለብን" ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ "የአመራር ተምሳሌትነት በተግባር የታየበትና ሕዝብን የሚያነሳሳ ነው" ሲሉ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
በእንግሊዝ ለንደን የሚኖሩት አቶ አለባቸው ደሳለኝ፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ "ትክክለኛ ወቅታዊና ቆራጥነት የታከለበት" ነው ሲሉ ገልጸውታል።
የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመቻው አካል መሆን እንዳለበትና የመንግስት አመራሮችም ግንባር ድረስ በመዝመት መስዋዕትነት መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
"ይሄ ወቅት የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን" ያሉት አቶ አለባቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገሩን ለማዳን መዝመት አለበት ብለዋል።
በጃፓን ቶኪዮ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሰይፈ ገብረሚካኤል በበኩላቸው "የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥሪ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እኔ ጦሩን አዋጋለሁ ብለው የተነሱ መሪዎችን አርአያ የተከተለ ውሳኔ ነው" ብለዋል።
በውጭ አገራት የምንኖር የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በጥሪው መሰረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።
"የነጻነት ምልክት" የሆነችውን ኢትዮጵያ መስዋዕትነት በመክፈል መከራውን እንድትሻገር የማድረግ ነጻ የሆነች አገርን ለሚመጣው ትውልድ ማስረከብ ይኖርብናልም ብለዋል።
በውጭም በውስጥም የሚኖሩ ሁሉ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ያላቸውን አቅም ተጠቅመው አገራቸውን በመደገፍ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።