ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የምትገነባው ዜጎቿ በየተሰማሩበት መስክ በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ነው

አዲስ አበባ ህዳር 14/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የምትገነባው ዜጎቿ በየተሰማሩበት መስክ በሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የሥራ ኢንተርፕራይዝና ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

የቢሮው ሠራተኞችና አመራሮች በግንባር መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው የአገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል።

ምክትል ከንቲባ እና የቢሮው ኃላፊ ጃንጥራር አባይ የውጭ ኃይሎችና የውስጥ ባንዳዎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየጣሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም መላው ሕዝብ እነዚህን ሃይሎች በመመከት አገሩን ማቆየትና ለትውልድ ማሸጋገር እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የምትገነባው ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት መስክ በሚያበረክተው አስተዋጽኦ በመሆኑ ሥራውን ማሳካት ከቻለ በግንባር እየተፋለመ ላለው ኃይል ትልቅ ድጋፍ መሆኑንም ነው አቶ ጃንጥራር የተናገሩት።

የምክትል ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ደረጃው ባይጨክን በበኩላቸው፤ ውጊያው ከአሸባሪው ቡድን ጋር ብቻ ሳይሆን አገራችንን ለማፍረስ ከቋመጡ ሃይሎች ጋር ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓርአያ በመሆን ያሳዩት ቁርጠኝነት ከሁሉም የሚጠበቅ ነው ያሉት ኃላፊው፤ እርሳቸውም ይህንኑ እንደሚከተሉ ገልጸዋል።

"አገር ለመበተን ከሚነሳ በላይ ጠላት የለም" ያሉት ደግሞ በቢሮው የመሥሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኃላፊ አቶ አስመሮም ብርሃኔ ናቸው።

ሕዝቡም ይህንን አገር አፈርሳለሁ ብሎ የመጣውን ኃይል በመመከት እስከመጨረሻው መደምሰስ ይኖርበታል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም