ቀጥታ፡

የዶክተር ዐቢይ አህመድ ውሳኔ የጀግንነት ተጋድሎ የፈጸሙ የኢትዮጵያ መሪዎችን ታሪክ የደገመ ነው -ምሁራን

ባህር ዳር ህዳር 14/2014 (ኢዜአ)"ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ አሸባሪውን ህወሓት ለመፋለም ወደ ግንባር መዝመታቸው የጀግንነት ተጋድሎ የፈጸሙ የኢትዮጵያ መሪዎችን ታሪክ የደገመ የተጋድሎ ውሳኔ ነው" ሲሉ የህግ ምሁራን ገለጹ።

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትህ ባለሙያዎች ማሰልጠኛና የህግ ምርምር ኢንስቲትዩት የህግ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ አበበ ካሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ መሪዎች በግንባር ዘምተው ድልን ማስመዝገብ የቆየ ባህላቸው ነው።

ከአድዋ ጦርነት በፊትም ሆነ በኋላ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚመጣ ጠላትን ህዝብን በማስተባበር በጀግንነት ተፋልሞ ድል መንሳት ከጥንት ጀምሮ የመጣ የኢትዮጵያዊያን ታሪክ መሆኑን ገልጸዋል።

"በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ጀግንነት ለወታደር ብቻ የተሰጠ አይደለም" ያሉት አቶ አበበ፣ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የመሪ ሚስቶችና ሴቶችም ጭምር የወታደራዊ ጥበብና ሳይንስ እውቀትን ተጠቅመው ድል የሚያስመዘግቡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ "በየዘመናቱ ሀገር የገጠማትን አደጋ ለመቀልበስ ህዝብን በማስከተል የጀግንነት ተጋድሎ የፈጸሙ የኢትዮጵያ መሪዎችን ታሪክ በዘመናቸው በመድገም ለአሁኑ ትውልድ ያጋሩበት ነው" ብለዋል።

"እንደ አንድ የሀገር መሪ አድርግ ብሎ ማዘዝና አድርጎ ማሳየት ውጤቱ የተለያየ ነው" ያሉት አቶ አበበ፣ "ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ' ማለታቸው ጊዜው የሁላችንንም መስዋዕትነት የሚጠይቅ ስለመሆኑ ጥሩ መሳያ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ውሳኔያቸው በግንባር ጠላትን አንገት ለአንገት እየተናነቀ ላለው ወታደር የማሸነፍ ቁርጠኝነትና ወኔን ከመሰነቅ ባለፈ ለህዝቡ ታላቅ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ነው አቶ አበበ የገለጹት።

በኢንስቲትዩቱ የህግ ተመራማሪ አቶ ይማም ሰይድ በበኩላቸው "የጠቅላይ ሚንስትሩ ውሳኔ የአሁኑ ትውልድ በታሪክ የሚያውቀውን የአባቶቻችንን ገድል የሚዘክር ነው" ሲሉ ነው የገለጹት።

በአድዋ፣ በማይጨው እና ሌሎች ጦርነቶች ኢትዮጵያ ያሸነፈችው መሪዎቻችን ከፊት ተሰልፈው በማዋጋታቸው መሆኑን ታሪክን ዋቢ አድርገው ተናግረዋል።

"ቢሮ ውስጥ ወንበር ላይ ተቀምጦ የሚያዋጋ መሪ ኢትዮጵያ አለመደችም" ያሉት አቶ ይማም፣ የዶክተር ዐቢይ ውሳኔ ኢትዮጵያ በየዘመኑ ግንባር ዘምቶ በመፋለም ጠላትን ድባቅ የሚመታ ጀግና መሪ የሚፈጠርባት አገር ስለመሆኗ አንድ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

"በውሳኔያቸው ከአሸባሪው ህወሓት ሃይል ጋር እየተካሄደ ያለውን ጦርነት በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የቆረጠ መሪ እንዳለን ዓለም ሊያውቅልን ይገባል" ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መዝመት መላ ኢትዮጵያዊያን አሸባሪውና ወሪውን ህወሀት ለመደምሰስ በአንድነት ወደ ግንባር በመትመም ከመሪያቸው ፊት እንዲሰለፉ ይበልጥ መነሳሳትን የሚፈጥር ውሳኔ መሆኑን የህግ ተመራማሪው ተናግረዋል።

በግንባር እየተፋለመ ላለው የመከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ሃይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና ወጣት የጀግነነት ወኔን በማላበስ የአሸባሪውን ግብአተ መሬት ለመፈጸም የሚያስችል ውሳኔ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የህግ ምሁራኑ እንዳሉት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚችለው ወደ ግንባር በመዝመት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ፊት መሰለፍ፣ የማይችለው ስንቅና ትጥቅ በማቅረብ ለሀገሩ ሉአላዊነት መከበር እስካሁን ካደረገው በላይ አስተዋጾ ማድረግ ይኖርበታል።

በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆችና ምሁራንም በገንዘብና በዲፕሎማሲው መስክ እያደረጉ ያለውን ተሳትፎ በማጠናከር ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት አደጋ ለማውጣት የበኩላቸውን እንዲወጡ ምሁራኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም