ኢትዮጵያ በጋራ የመልማት መርኋን በማጠናከር በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ይኖርባታል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በጋራ የመልማት መርኋን በማጠናከር በምስራቅ አፍሪካ ጠንካራ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ይኖርባታል
ኅዳር 14/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ አብሮ የመልማት መርኋን በማጠናከር ጠንካራ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን ይኖርባታል ሲሉ የአፍሪካና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰሩ ሳሙኤል ተፈራ ተናገሩ።
ረዳት ፕሮፌሰሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያ ባለፉት የመንግሥት አስተዳደሮቿ ለአፍሪካዊያ ነፃነት ብርቱ ትግል ማድረጓን አውስተዋል።
በሁለት ጎራ ተከፍሎ የነበረውን የሞኖሮቪያና ካዛብላንካ ቡድን ወደ አንድ በማምጣትም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ጉልህ ድርሻ እንደነበራት ጠቁመዋል።
በዚህም አፍሪካዊያን በምጣኔ ሃብት፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና በፖለቲካዊ መስኮች በጋራና በትብብር እንዲሰሩ ተግባር ማከናወኗን ነው የገለጹት።
በአህጉራዊ የትብብር በጋራ የመልማት መንፈስ እንዲቀጥል የያዘችውን አቋም ማደግ እንዳለባት መክረዋል።
ለአህጉሪቱ ያሳረፈቻቸውን ጉልህ አሻራዎች በማስቀጠልም ራሷን ከታማኝ አጋር ወደ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ማሸጋገር ይኖርባታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ስለምታራምደው አብሮ የመበልጸግ ፓለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ እድገት የተመለከቱ ራዕዮቿን ለጎረቤት አገራት ግልጸኝነት መፍጠር እንደሚያስፈልጋትም ገልጸዋል።
ይህንን የኢትዮጵያ ራዕይ ለጎረቤት አገራት በራሳቸው ቋንቋ እንዲረዱ የሚያስችሉ የመገናኛ ብዙሃን ተደራሽነትን ማስፋት እንደሚገባም ነው ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል የጠቆሙት።
ምዕራባዊያን በአፍሪካ ተላላኪ መንግሥታት እንዲኖሩ በማድረግ የአፍሪካ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ እንዲኮሰምን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ምዕራባዊያኑ የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በዘረጓቸው የእርዳታና መሰል ተቋማት አፍሪካ በተጽዕኖ ስር እንድትወድቅና የእነርሱን ዓላማ ለማስፈጸም እየሰሩ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ አፍሪካዊያን ከሚጣልባቸው ጫና ለመውጣት ትላልቅ የሚባሉ አገራዊና አህጉራዊ ፕሮጀክቶችን በትብብር በማልማት ራሳቸውን ነፃ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም የጀመራቸውን የትብብር ማዕቀፎች በማስፋት ከቀጣናው አገራት ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማስቀጠል እንደሚገባው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከውጭ ኃይሎች እየደረሰባት ያለውን ያልተገባ ጫና ለመቋቋም ሁሉም ዜጎቿ ከመንግሥት ጋር በመሆን አንድነቱን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ።