በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሪነት፤ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ የአድዋ ድል ይደገማል - ኢዜአ አማርኛ
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሪነት፤ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ የአድዋ ድል ይደገማል
አዲስ አበባ፣ ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሪነት በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ የአድዋ ድል ይደገማል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የደብረ ብርሃን ጠቅላላ ሆስፒታል የህክምና ዶክተሮች ተናገሩ።
"ለአፍሪካዊያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" በብዙ አፍሪካውያን ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ የድል ጉዟችንን ያፋጥናልም ብለዋል።
የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተነሳውን የህወሃት አሸባሪ ሃይል ለመፋለም ጀግናውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ለመምራት ወደ ግንባር እንደሚዘምቱ ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ለአገራቸውና ለህዝባቸው ያላቸውን ቆራጥ አመራር በተግባር ያሳየ በመሆኑ ሁላችንንም አኩርቷል፤ በርካቶችም ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ አድርጓል ብለዋል የደብረ ብርሃን ሆስፒታል ዶክተሮች።
በሆስፒታሉ ጠቅላላ ሃኪምና የጥራት ክፍል ሃላፊ ዶክተር ክንዴ ሞላ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ግንባር ድረስ መዝመት ለሌሎች ኢትዮጵያውያን የሞራል ስንቅና የወኔ ትጥቅ ሆኗል ብለዋል።
በመሆኑም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሪነት በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ የአድዋ ድል ይደገማል ብለዋል።
በአድዋ ጦርነት ወቅት ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ "ክተት ሰራዊት" ብለው ግንባር ድረስ ዘምተው ጠላትን ተፋልመው በማሸነፍ ታሪክ ከሰሩ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለተመሳሳይ ድል የተነሱ ቆራጥ መሪ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሆስፒታሉ የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ጌታቸው ይልማ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመት ሁላችንም ለአገራችን ዘምተን ድል እንድናስመዘግብ አነሳስቶናል ብለዋል።
የደብረ ብርሃን ጠቅላላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ዳግም ሽመላሽ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ሲዘምቱ ከማየት በላይ ሌላ የአገር ፍቅር መግለጫ የለም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሌለች ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት ቀርቶ በህይወት የመኖር ተስፋም ስለሚጨልም ሁላችንም የመሪያችንን ፈለግ ተከትለን አገራችንን እንጠብቃለን ብለዋል።
ኢትዮጵያን ደካማና እንደፈለጉ የሚገዟት ሀገር ለማድረግ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እያለ አሸባሪ ቡድንን የሚደግፉ ሃይሎችን በተባበረ ክንድ ልንመክት ይገባልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በግልጽ የምታንጸባርቀው "ለአፍሪካዊያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" አቋም በብዙ አፍሪካውያን ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም መሰረት የአፍሪካውያን የነፃነት መገለጫ መሆኗን ገልጸው ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳዩትን ያልተገባ ጣልቃ ገብነት አፍሪካውያን መቃወማቸውን መልካም ጅምር ብለውታል።
በመሆኑም አፍሪካውያን "በቃ! እጃችሁን ከኢትዮጵያ ላይ አንሱ" ማለት መጀመራቸውና የኢትዮጵያ አቋም ተቀባይነት ማግኘቱ የድል ጉዟችንን ያፋጥናል ብለዋል ዶክተሮቹ።