ቀጥታ፡

በአደጋ መከላከልና መቆጣጠር የሰለጠኑ ወጣቶች የአዲስ አበባን ሰላምና ደህንነት እየጠበቁ ነው

ህዳር 14 / 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ያሰለጠናቸው ወጣቶች የአዲስ አበባን ሰላምና ደህንነት እየጠበቁ ነው።
ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ማህበረሰቡ አደጋን መከላከልና ራሱን መጠበቅ እንዲችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰለሞን ፍስሃ፤ በመዲናዋ በገበያ ቦታዎች፣ የነዳጅ ማደያዎች እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ሀዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች ላይ ልዩ ጥበቃና ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም ለማህበረሰቡ የጥንቃቄና አደጋን ቀድሞ የመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ተከናውኗል በቀጣይም ይከናወናል ነው ያሉት።

በተለይም ወጣቶች በአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ላይ የቅድመ መከላከል ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ኮሚሽኑ በአደጋ መከላከልና መቆጣጠር ያሰለጠናቸው ወጣቶች ከኮሚሽኑ አባላት ጋር በመሆን በቅንጅት የአዲስ አበባን ሰላምና ደህንነት እየጠበቁ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን ያለንበት ወቅት የእሳት አደጋ ተጋላጭነት የሚጨምር በመሆኑ የጥንቃቄና የቅድመ መከላከል ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

የአየር ሁኔታ ትንበያ እንደሚያመለክተው ነፋሻማው አየር እስከመጪው መጋቢት ወር የሚቀጥል በመሆኑ በተለይም የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል።

በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ላሉ ከ800 በላይ አመራሮች ጋር የመጀመሪያ ደረጃ የአደጋ መከላከል ሥልጠና በመስጠት ከኮሚሽኑ ጋር እንዲሰሩ መደረጉን ተናግረው በየትኛውም አካባቢ አደጋ ቢያጋጥም  በነፃው የስልክ መስመር 939 አስቸኳይ ጥሪ አድርጉልን ብለዋል አቶ ሰለሞን።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም