ለሠራዊቱ ያለንን የደጀንነት ሚና አሸባሪው ህወሓት እስኪደመሰስ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ለሠራዊቱ ያለንን የደጀንነት ሚና አሸባሪው ህወሓት እስኪደመሰስ ይቀጥላል
ህዳር 14/2014/ኢዜአ/ ለጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን የደጀንነት ሚና አሸባሪው ህወሓት እስኪደመሰስ ድረስ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው እናቶች የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ግዳጃቸውን በድል እንዲያጠናቅቁ የሞራል የሰንቅ ድጋፍ በመስጠት በደጀንነታቸው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ለመከላከያ ሠራዊቱና ለፀጥታ አካላቱ እያደረጉ ያሉትን የስንቅ ዝግጅት እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።
ወይዘሮ ጽጌረዳ ሽጉጤ "ለአገር መከላከያ ሠራዊት የምናደርገው ድጋፍ ጁንታው ጠፍቶ እስክንገላገል ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
ወይዘሮ ጽጌረዳ ከውስጥና ከውጭም የተቃጣብንን ወረራ በመመከት ጦርነቱን በአሸናፊነት እንደምናጠናቅቅ ጥርጥር የለውም ብለዋል።
በግንባር ከጠላት ጋር እየተፋለመ ለሚገኘው የጸጥታ ኃይል ተጨማሪ አቅም ለመሆን በስንቅ ዝግጅት አጋርነታችንን እያሳየን እንገኛለን ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሙሉ አየለ ናቸው።
አንደ አስፈላጊነቱ ግንባር ድረስ ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ወይዘሮ አይናለም ግዛው በበኩላቸው ከስንቅ ድጋፍ በተጨማሪ እስከ ግንባር ለመዝመት ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።
ከአገር በላይ ምንም ነገር የለምና ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም የሕልውና ዘመቻውን ዛሬውኑ ሊቀላቀል ይገባል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ግንባር እንደሚዘምቱ እና ሁሉም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የእርሳቸውን ፈለግ እንዲከትል ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።