ቀጥታ፡

ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

ህዳር 14 / 2014 (ኢዜአ) ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እንዲያገለግሉ በክልሉ ምክር ቤቱ ተሾሙ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተሾሙት አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል 11ኛው ክልል ሆኖ ዛሬ በይፋ መመስረቱን ተከትሎ ነው።

የክልሉ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የነበሩት ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በመመረጥ በምክር ቤቱ ቃለ መሀላ ፈጽመዋል።

ዶክተር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው እያገለገሉ ይገኙ ነበር።የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮ እና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ ነዋሪዎች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ የራሳቸውን ክልል ለመመስረት የሚያስችላቸውን ድምጽ መስጠታቸው ይታወሳል።

በዚህ መሰረት የክልሉ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የክልል ምስረታውን አካሂዷል።

ዛሬ በከፋ ዞን ቦንጋ ከተማ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባካሄደው ጉባኤ የክልሉ ምክር ቤት አባላት የክልሉን ህገ-መንግስት በሙሉ ድምጽ አጽድቀውታል ።

በጉባኤው የክልሉ ምክር ቤቱ አባላት ለህገ መንግስቱ ታማኝ በመሆኑን የክልሉን ህዝብ ለማገልገል ቃለ መሀላ የፈፀሙ ሲሆን አፈጉባኤና ምክትል አፈጉባኤም መርጠዋል።

በዚህ መሰረት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል አቶ ወንድሙ ኮርታ የክልሉ ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነው የተመረጡ ሲሆን ወይዘሮ ገነት መንገሻ ደግሞ ምክትል አፈጉባኤ ሆነው በመመረጥ ቃለመሃላ ፈጽመዋል።

በዛሬው ዕለት አምስቱ ዞኖች እና አንዱ ልዩ ወረዳ ከደቡብ ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመሥረታቸውን በመደገፋቸው ለኢትዮጵያ ፌድራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አስራ አንደኛው ክልል ሆነው በይፋ ተመስርተዋል።

የክልሉ የስራ ቋንቋ አማርኛ እንዲሆን በሙሉ ድምጽ የጸደቀ ሲሆን÷ የዞን መዋቅሮች ደግሞ የራሳቸውን ቋንቋ እንደሚገለገሉ ተገልጿል።የዘመናት በክልል የመደራጀት ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለሰጠው የለውጥ መንግስት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ምስጋና ችረዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝቦቹ ባላቸው ሥነልቦናዊ አንድነት፣ በቋንቋ፣ በታሪክ፣ በባህላዊ እሴቶች እና በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ መቀራረባቸው በአንድነት በክልል እንዲደራጁ ምክንያት ሆኗል።

ክልሉ 39 ሺህ 64ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ሲኖረው የክልሉ ሕዝብ በዋናነት በጥምር ግብር እና በአርብቶ አደርነት የሚተዳደሩ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።

በክልሉ እንደ ጨበራ ጩር ጩራ፣ ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ ያሉ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦች ይገኛሉ።

በሸካ ዞን የሚገኘው ጥብቅ ደን፣ የከፋ የጫካ ቡና እንዲሁም ሰፊ ሽፋን ያለው ደን የዚሁ ክልል የተፈጥሮ ሀብት ናቸው።

በዳውሮ ዞን የሚገኘው የንጉሥ ሃላላ የድንጋይ ካብ ሌላኛው የቱሪስት መስህብ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

በመርሀ ግብሩ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።

-አካባቢህን ጠብቅ

_ ወደ ግንባር ዝመት

_ መከላከያን ደግፍ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም