ቀጥታ፡

ከምን ጊዜው በላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጎን የምንቆምበት ወቅት ነው-የአሶሳ ነዋሪዎች

አሶሳ፣ ህዳር 14 / 2014 (ኢዜአ)  ኢትዮጵያዊያን መቼም ቢሆን ለቅኝ ገዥዎች እንደማይንበረከኩ በተግባር ካረጋገጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ጎን በመሰለፍ የሀገርን ሉዓላዊነት እናስከብራለን ሲሉ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የአሶሶ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ዘምተው የሕልውና ጦርነቱን ለመምራት መወሰናቸው ለሀገር ሕልውናና ሉዓላዊነት መከበር ያላቸውን ፅኑ አቋም  በተግባር ያረጋገጠበት ነው።

የእሳቸው ውሳኔ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን ከምንጊዜው በበለጠ ለአንድነት የሚያነሳሳና ለሀገሩ ያለውን ቀናኢነት ዛሬም እንደጥንት አባቶች ይበልጥ በተግባር  የሚያረጋግጥበት ወቅት ነው ብለዋል።

በአካባቢያቸው የአሸባሪው ህወሓት ተልዕኮ አስፈጻሚዎችን አድነው ለፀጥታ ኃይል ከማስረከብ ጀምሮ ግንባር ለመዝመት ዝግጁ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ አረጋግጠዋል ።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ኢብራሂም አዙቤር እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ  ከዛሬ ጀምሮ ወደ ጦር ግንባር ዝምተው የሕልውና ጦርነቱን ለመምራት መወሰናቸው  ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ ያላቸውን ፅኑ አቋም  በተግባር ያረጋገጠ ነው ።

"የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ለሀገር ሕልውና እና ሉዓላዊነት መከበር ያላቸውን ፅናት በተግባር ያሳየ ነው" ያሉት አቶ ኢብራሂም ውሳኔው ኢትዮያውያንን  ከምንጊዜውም በላይ በአንድነት ተነስተው በሕልውና ዘመቻው እንዲሳተፉ መነሳሳትን የየሚፈጥር ነው።

"ኢትዮጵያውያን በታሪክ ለውስጥ ባንዳዎችና ለውጭ ወራሪ ኃይሎች እጅ ሰጥተው አያውቁም" ያሉት  አቶ ኢብራሂም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔም ይህንኑ በተግባር ያረጋገጠ በመሆኑ የኢትዮጵያውያን ከጎናቸው በመቆም የሀገርን ሉዓላዊነትን የምናስከብርበት ወቅት አሁን ነው" ሲሉ በአጽኖት ተናግረዋል ።

"ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ግንባር እንዲሚዘምቱ የገለጹበት የትናንትናው ቀን በሕይወቴ በእጅጉ የተደሰትኩበት እለት ነው" ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ መምህርት ብርሃኔ በቀለ ናቸው።

"አሸባሪው ህወሓት በውጪና በውስጥ የጥፋት ኃይሎች ታግዞ የሚፈጽምብን ግፍ በእጅጉ ቁጭት ፈጥሮብኛል" ያሉት መምህርት  ብርሃኔ  "ድርጊቱ በቁጭት ተነሳስተን ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ አንድነታችንን እንድናጠናክር አድርጓል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦር ግንባር ለመዝመት መወሰናቸው ለሀገርና ለህዝብ መስዕዋት ለመክፈል ያላቸውን ፅናት ያሳየ በመሆኑ ከምን ጊዜውም በላይ ከጎናቸው መቆም ያለብን ጊዜ አሁን ነው " ሲሉም አመልክተዋል ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ግንባር መዝመት መላውን ሕዝብ በማነሳሳት የሕልውና ጦርነቱ ባጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ እየተደረገ ላለው ሁሉን አቀፍ ትግል ስኬት አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ቢራራ ካሳ ናቸው፡፡

"የጠቅላይ ሚኒስተሩ ወሳኔ በአሸባሪው ህወሓት ሀገር መደፈሯ ቁጭት የፈጠበት መላው ኢትዮጵያዊ በአንድነት ተነሳስቶ እንዲዘምት የሚያደርግ ነው" ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ቢራራ ገለጻ ወደ ግንባር ዘምተው የሽብር ቡድኑን ለመፋለም ወስነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀድሞም በውትድርና ዓለም ተሰልፈው የሀገርን ሉዓላዊነት ያስከበሩ የጦር መሪ እንደነበሩ የገለጹት ደግሞ አቶ አበበ አሰጌ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ለመዝመት መወሰናቸው ለሌላው ኢትዮጵያዊ አርዓያ መሆኑን ጠቁመው፤ "ሁላችንም ግንባር ከመዝመት ጀምሮ በየአካባቢያችን የተሰገሰጉ የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዦችን በመታገል ጠቅላይ ሚኒስትሩን መደገፍ ዋነኛ ስራችን ሊሆን ይገባል " ብለዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም