ቀጥታ፡

በቀን ፋኖስ የማብራት ትዕይንተ ህዝብ የፊታችን ሀሙስ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን እውነት እያዩ እንዳላዩ የሚመስሉ ምዕራባዊያንን ለመቃወም በቀን ፋኖስ የማብራት ትዕይንተ ህዝብ የፊታችን ሀሙስ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ "የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ጥምረት ለኢትዮጵያ ህዝብ" አስታወቀ።

የጥምረቱ ፕሬዚዳንት ጋሻው ሽባባው በመጪው ሀሙስ የውጭ ጣልቃ ገብነትን የሚቃወሙ የተለያዩ ትዕይንተ ህዝቦች ይከናወናሉ ብለዋል።

ትዕይንት ህዝቡ በዋናነት በመጪው ሀሙስ ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ መነሻውን አራት ኪሎ አድርጎ የሚከናወን ነው።

በመቀጠል በዚህ ትዕይንተ ህዝብ  ላይ የሚካፈሉ ዜጎች  ወደ አሜሪካና እንግሊዝ ኤምባሲዎች  በመሄድ ተቃውሟቸውን ያሰማሉ ተብሏል፡፡

የሃይማኖት አባቶች ጭምር በተገኙበት በቀን ፋኖስ በማብራት ምዕራባዊያን የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስትን እውነትና ፍላጎት እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉበትን አካሄድ በመቃወም ልዩ ልዩ መልእክቶች ይተላለፋሉ።

በእለቱ  ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ ለ10 ደቂቃ ያህል መኪኖች መብራት በማብራት ክላክስ እያደረጉ ተቃውሞውን ይደግፋሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም