ቀጥታ፡

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር አቅንተው እኔ ቤት የምቀመጥበት አንድም ምክንያት የለም"

ህዳር 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር አቅንተው እኔ ቤት የምቀመጥበት አንድም ምክንያት የለም፣ ያለኝን የውትድርና ጥበብ ተጠቅሜ ጠላትን ድል ለማድረግ ዝግጁ ነኝ " ሲሉ ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ ገለጹ፡፡

ብርጋዴር ጀነራል ካሳዬ ጨመዳ ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር የስልክ ቆይታ አድርገዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ማቅናት ግንባር ላይ እየተዋደቀ ለሚገኘው ሰራዊት ከፍተኛ መነሳሳትና የሞራል ስንቅ ይሆነዋል ብለዋል፡፡

ጀነራሉ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ውሳኔ መወሰናቸው ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠላትን ድል ለማድረግ ያግዛታልም ብለዋል፡፡

ሰራዊቱ መሪው ጎን ሆኖ ሲዋጋ እንዴት ድል ማድረግ እንዳለበት ያውቅበታል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

"እኔም አንድ ልጄን ይዤ በማንኛውም ሰዓት መከላከያ በሚፈልገው ቦታ ለአገሬ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል፡፡

ግንባር በመሄድ ያለኝን የውትድርና ጥበብ ተጠቅሜ ጠላትን በመደምሰስ ኢትዮጵያን ለማዳን ተዘጋጅቻለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

መላው የኢትዮጵያ ህዝብም የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርዓያ በመከተል ወደ ግንባር ማቅናት ያለበት በመዝመት ሌላው ደግሞ በመደገፍ ለአገሩ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታልም ብለዋል፡፡

በተለይም የቀድሞ ሰራዊት አባላት ለዚህ ጥሪ ግንባር ቀደም በመሆን ትናንት ለአገራቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት ዛሬም መድገም አለባቸው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

“ኢትዮጵያ” የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን! ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጀምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

-አካባቢህን ጠብቅ

_ ወደ ግንባር ዝመት

_ መከላከያን ደግፍ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም