የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ለመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ለመከላከያ ሠራዊትና ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

ህዳር13/2014 (ኢዜአ) የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች በአፋር ግምባር ተገኝተው ለአገር መከላከያ ሰራዊትና በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ።
የተደረገው ድጋፍም ደረቅ ሬሽኖች፣ የመጠጥ ውኃ፣ አልባሳትና የዕለት ደራሽ ምግቦች ናቸው።
ድጋፉን ካደረጉት መካከል ጋዜጠኛ ደረጀ ሃብተወልድ፤ በአፋር ግምባር በመጀመሪያ ዙር ከ600 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው ድጋፍ ማድረጉን ተናግሯል።
አሁን ደግሞ ለሁለተኛ ዙር 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን ጠቁሟል።
ጋዜጠኛ ደረጀ ከተባባሪዎቹ ባሰባሰበው ገንዘብ ግምባር ላይ አየተፋለሙ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት የተለያዩ አልባሳትና የመጠጥ ውኃ ማቅረቡን ገልጿል።
በአገር ውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን በሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሳይደናገሩ ለኢትዮጵያ ህልውና እየተዋደቀ ላለው ሠራዊትና ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲደግፉ ጥሪ አቅርቧል።
የሀረሪ ክልልም በአፋር ግምባር በመገኘት ከአንድ ሚሊዮን ብር የሚልቅ ግምት ያለው የምግብና ንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ለሁለተኛ ዙር ድጋፍ አድርጓል።
የክልሉ የንግድ ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ብሽራ አሊ፤ ክልሉ 500 ካርቶን ቴምር፣ 132 ካርቶን ወተትና ለሴቶች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የክልሉ ሕዝብ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ሆኖ ድጋፉን ያጠናክራልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን ማገዝ የሚያስችል የምግብና አልባሳት ድጋፍ አድርጓል።
ኢሳት ለተፈናቃይ ወገኖች ዱቄት፣ መኮሮኒ፣ ፓስታና የተለያዩ አልባሳት ድጋፍ ማድረጉን የቴሌቪዥኑ ተወካይ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ቀጸላ ገልፃለች።
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚችለው አቅም ሁሉ ለችግር የተዳረጉ ዜጎችን መደገፍ እንዳለበት መልእክቷን አስተላልፋለች።
ድጋፉን የተረከቡት የካሳ ጊታ ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ አቶ መሓመድ ኑር ሳሊም አሻባሪው በከፈተው ጦርነት ብዙ ዜጎች ለችግር ተዳርገዋል ብለዋል።
በካሳ ጊታ ግምባር አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ከአካባቢው በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ጠቅሰዋል።
ከተፈናቃዮቹ መካከል በርካታዎቹ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን ገልጸው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ከአካባቢው የተፈናቀሉት ወገኖች እንደሚገልጹት አሻባሪው ህወሃት በድንገት ወረራ በመፈፀሙ ምንም ነገር ሳይዙ ቤታቸውን ለቀው ወጥተዋል።
ከተፈናቃዮቹ መካከል ጨቅላ ህጻናት የያዙ እናቶች፣ ህፃናትና አረጋዊያን በመኖራቸው የዕለት ደራሽ እርዳታ እንዲቀርብላቸው ጠይቀዋል።