የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ታሪክ ለማስቀጠል የአሁኑ ትውልድ ትልቅ አደራ ተጥሎበታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ታሪክ ለማስቀጠል የአሁኑ ትውልድ ትልቅ አደራ ተጥሎበታል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን የአሸናፊነት ታሪክ ለማስቀጠል የአሁኑ ትውልድ ትልቅ አደራ የተጣለበት መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በክልሉ የፓርቲው አባላትና የመንግስት ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደማቸውን ለግሰዋል።
በአሸባሪው ሕወሃት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን የህልውና አደጋ ለመመከት ኢትዮጵያዊያን በበጋራ መቆማቸውን በተግባር አረጋግጠዋል።
ህዝቡ ለሰራዊቱ ስንቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ አለኝታነቱን በማሳየት ላይ ይገኛል።
በዛሬው እለትም በኦሮሚያ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አባላትና የመንግስት ሰራተኞች ለአገር መከላከያ ሰራዊት ደማቸውን ለግሰዋል።
በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ልዩ ረዳት አቶ ብርሃኑ ፈይሳ፤ ከውስጥና ከውጭ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የቀናጀ ጦርነት በጋራ ክንዳችን መመከት አለበን ብለዋል።
የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ታሪክ ለማስቀጠል ይህ ትውልድ ትልቅ አደራ የተጣለበት በመሆኑ ለአሸናፊነት መዘጋጀት አለበት ነው ያሉት።
ለመከላከያ ሰራዊት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት አቶ ብርሃኑ አሁን ላይ የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ ሲሆን የደም ልገሳ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
ለሰራዊቱ ደም የለገሱ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች፤ ለኢትዮጵያ ህልውና በሚደረገው ትግል በሁሉም መስኩ ድጋፍ፣ እገዛና ትብብሩ መቀጠሉን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል 5 ሺህ 600 ዩኒት ደም ለማሰባሰብ ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን በዛሬው እለት ለሁለተኛ ዙር የደም ልገሳ ተከናውኗል።