የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለሠራዊቱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለሠራዊቱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ህዳር 13/2014 (ኢዜአ) የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ለሠራዊቱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የኮሌጁ ማህበረሰብ፣ በመከላከያ የሰላም ማስከበር ማዕከል አባላትና አመራሮችም ለሰራዊቱ ደማቸውን ለግሰዋል።
የኮሌጁ ዲን ተወካይ ኮሎኔል ሚዛን ውዳሠር፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ በልጆቿ መስዋእትነት መሻገሯን ጠቅሰው አሁንም በቆራጥ ልጆቿ ክብሯ ተጠብቆ ትቀጥላለች ብለዋል።
አሁን የገጠማትን ፈተና ለማለፍ ዜጎች ያለምንም ልዩነት ሁለንተናዊ ተሳትፏቸውን ሲያጠናክሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በአገር ህልውና የማስከበር ዘመቻው ሠራዊቱ በቆራጥ መስዋእትነት ሕይወቱን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም መላው የኢትዮጵያ ህዘብ ሁለንተናዊ ድጋፉን ማጠናከር አለበት ያሉት ኮሎኔል ሚዛን፤ የመከላከያ አዛዥነትና ስታፍ ኮሌጅ ከቁሳቁስ ድጋፍ መተጨማሪ ደሙን ለግሷል ብለዋል።
በህልውና ማስከበር ሂደቱ ጉዳት ለገጠማቸው የሰራዊት አባላት 168 ሺህ ብር እንዲሁም ለተፈናቀሉ ወገኖች 426 ሺህ ብር በድምሩ 594 ሺህ 590 ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ቆንጂት ደበላ ኮሌጁ በአይነት ሀብት አሰባስቦ ድጋፍ በማድረጉ አመስግነዋል።
በክፍለ ከተማው ለህልውና ዘመቻው የሚውል ከ18 ሚሊዮን በላይ ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸው፤ ከደጀን እስከ ግንባር ያለው ድጋፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ከድጋፍ መርሃ-ግብሩ ባሻገርም የኮሌጁ አባላት፣ የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የሠራዊቱ አባላትና አመራሮች ደም ለግሰዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው ደም የለገሱ የሠራዊቱ አባላትም ለኢትዮጵያ ሕልውና ደም፣ ገንዘብና ሕይወታቸውን ለኢትዮጵያ ህልውና ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሻለቃ መለሰ ደማችንም ህይወታችንንም ሆነ ያለንን ነገር አገርና ትውልድ እንዲቀጥል ማንኛውንም ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው ህዝቡ አሁን ያለውን ግለት ጠብቆ እስከመጨረሻው ድረስ አብሮን ሊሰለፍ ይገባል ብለዋል።
"ኢትዮጵያዊያን አንድነታችን፣ ሉዓላዊነታችንና ጀግንነታች ይታወቃል'' በኢትዮጵያዊነታችን የማይደራደር እና መላው ኢትዮጵያዊያን ባለን አቅም ደም በመለገስ ለሰራዊቱ ድጋፍ በማድረግ
የኋላ ደጀንነታችሁን እንድታረጋግጡ'' በማለት ጥሪያቸውን ያቀረቡት ደግሞ መቶ አለቃ ጸዳለ ሞላ ናቸው።
ሻለቃ ስንታየሁ መንግስቱ በበኩላቸው "ደም መስጠት ለእኔ ምንም ማለት አይደለም ከዚህም በላይ ግንባር ድረስ በመሄድ ጓዶቻችን እየተሳተፉ ነው ያሉት። እስከ ህይወት መስዕዋትነት ድረስ ዝግጁ ነኝ ።በዘረኝነት በጎጥ ሳይከፋፈል አሁን እንደተሳተፈው ሁሉ እስከመጨረሻው ድረስ መቀጠል አለበት" በማለት ተናግረዋል።