አብሮነትና አንድነትን ለማጠናከር ሀገራዊ ባህሎችና እሴቶችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አብሮነትና አንድነትን ለማጠናከር ሀገራዊ ባህሎችና እሴቶችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል
ህዳር 13/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የቆየውን የመቻቻል፣ አብሮነትና አንድነትን ለማጠናከር ሀገራዊ ባህሎችና እሴቶችን በማጎልበት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተመለከተ።
"16ኛው የጉሚ በለል ውይይት "የመቻቻል ባህል አንድነትን ለማጠናከር ያለው ፋይዳ" በሚል መሪ ሃሳብ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት ተካሄዷል።
ውይይቱ የተካሄደው በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ27ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረውን የመቻቻል ቀን ምክንያት በማድረግ ነው።
በኢትዮጵያ የቆየውን ሀገራዊ የመቻቻልና አብሮነት እሴቶችን በማጎልበት ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማጠናከር ስለሚቻልበት ሁኔታ በውይይት ተነስቷል።
የውይይቱን መድረክ ያስተባበሩት የኦሮሞ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ስንታየሁ ቶላ፤ መቻቻል የዓለም ህዝቦችን ባህልና አኗኗር ማድነቅና ማክበር ስለመሆኑ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መቀመጡን ጠቅሰዋል።
አቶ ስንታየሁ አክለውም በማህበረሰቡ መካከል መቻቻልና አብሮነትን ለማስፈንና ለማጠናከር የዩኔስኮ አምስቱ ተግባራት ገቢራዊ ሊደረጉ ይገባል ብለዋል።
"የህግ የበላይነትን ማስፈንና የተላለፈን የሚገባውን ቅጣት መስጠት፣ ትምህርትን ማስፋፋት፣ ማህበረሰብን ለመረጃ ተደራሽ ማድረግ፣ የግለሰቦችን የንቃት ደረጃ ማሳደግ እንዲሁም ለችግሮች አካባቢያዊና ሀገራዊ መፍትሔ መስጠት" የዩኔስኮ አምስቱ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ለውይይቱ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና አማካሪ አቶ ሌኒን ቁጦ እንዳሉት፤ እንደ ማህበረሰብ የራስን የቆየ እሴት በአግባቡ አለመጠቀም ሀገርን ለችግር ይዳርጋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች ለብዙ ሺህ ዓመት በመቻቻል እና በአብሮነት የኖሩበትን ቁልፍ እሴቶችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የኦሮሞ ሕዝብም በባህሉና በቆየው የገዳ ሥርዓቱ መቻቻልንና አቃፊነትን በማስቀጠል ከሌሎች ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር እንዴት አብሮ ሲኖር እንደነበርና ለወደፊቱም በልዩነት መሐል ጠንካራ አንድነትን ለሀገራዊ ግንባታ ማዋል በሚቻልበት ዙሪያ ተሳታፊዎች ሀሳብ አንስተዋል።
ለተነሱት ሀሳቦችና ጥያቄዎችም ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በዚሁ 16ኛው የጉሚ በለል ውይይት የባህል ዘርፍ ባለሙያዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና አባ ገዳዎች ተሳትፈዋል።
የጉሚ በለል ውይይት በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተዘጋጀ ባለሙያዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የሚሳተፉበት መድረክ መሆኑ ተመልክቷል።