ኢትዮጵያን የማዳን የዜግነት ሃላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን የማዳን የዜግነት ሃላፊነታችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን
አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/2014(ኢዜአ) አንድነታቸውን በማጠናከር ለመጪው ትውልድ ሉዓላዊት ኢትዮጵያን ለማስረከብ የዜግነት ድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን የተለያዩ ክልሎች ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን ወቅታዊ የሕልውና ስጋት ለመመከት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የመከላከያ ሠራዊቱን በመደገፍና በዘመቻውም በመሳተፍ የዜግነት ድርሻውን እየተወጣ ይገኛል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የተለያዩ ክልሎች ነዋሪዎችም ወቅቱ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የጋራ አቋም በመያዝ አንድነታቸውን በማጠናከር ለትውልዱ ሉዓላዊት አገር የማስተላለፍ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ አገሪቷን ለማፍረስና ሕዝቧቿንም ለመበታተን የሚታትሩ ኃይሎችን በመታገል ኢትዮጵያን የማዳን ሃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በምስረቅ ወለጋ የነቀምቴ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሃኒም በላይ አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ፈተና ውስጥ እንደሆነች እና ብዙ መስዋዕትነት እየተከፈለ መሆኑን ገልጸው "በተሰማራንበት የስራ መስክም ሆነ ሃላፊነት ግዴታችንን መወጣት ነው ያለብን" ብለዋል።
የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳንኤል ወርቁ በሰጡት አስተያየት ሁሉም ማህበረሰብ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለባቸው በመጥቀስ ግንባር ሄዶ መዝመትና መፋለም ያልቻለው በየአካባቢው ስንቆችን በማዘጋጀት አለኝታነታችንን ማሳየት አለብን ብለዋል።
"እኛ አገር ግንባታ ላይ ነን እና ምናልባት አሁን እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ቢያጠናክሩን እንጂ ወደኋላ የሚያስብሉ አይደሉም ያሉት ደግሞ የጅማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አህመድ መሃመድ ናቸው።
ስለሆነም በነፍሳችን፣ በደማችን፣ የማንችል ደግሞ መረጃ በመስጠትና በአካባቢያችን በመደራጀት ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን ብለዋል።
በየአካባቢው ያለው ማኅበረሰብ ለሠራዊቱ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር አካባቢውን ከጠላት ነቅቶ መጠበቅ እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።
አስተያየት ሰጪዎቹ በየአካባቢያቸው የትግሉ አካል በመሆን አገሪቷ ወደ ቀድሞ ሠላምና አንድነቷ እንድትመለስ የበኩላቸው እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
አገር በምታቀርበው ጥሪ ተሳታፊ በመሆን የዜግነት ድርሻቸውን ለመወጣት ቁርጠኞች መሆናቸውንም ነው የገለጹት።