ቀጥታ፡

የህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ለማደግ ያስቀመጠችውን መርህ የሚያቀላጥፍ ፕሮጀክት ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/2014 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከቀጠናው አገራት ጋር ተሰናስላ ለማደግ ያስቀመጠችውን መርህ የሚያሳልጥ ፕሮጀክት መሆኑን የአፍሪካ እና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ የአባይ ውሃ ምንጭ ብትሆንም ሳትጠቀምበት ዘመናት ተሻግረው አሁን ላይ ለህዝብ ብርሃን እንዲሆን ግድብ እየገነባች ትገኛለች።

አባይ ኤሌክትሪክ እያመነጨልኝ ይፍሰስ በማለት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመገንባታ ላይ ትገኛለች።

ይሁን እንጂ በተለይም ሁለቱ የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት “ምን ሲሆን በአባይ ላይ ግድብ ይሰራል” በማለት  የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ፕሮጀክቱን ለማስተጓጎል ሲሞክሩ ይታያል።

የአፍሪካ እና እስያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተፈራ ህዳሴ ግድብ የግጭት ምክንያት ሳይሆን በጋራ የመልማትና የጋራ ተጠቃሚነት እቅድ ያነገበ ፕሮጀክት እንደሆነ ያስረዳሉ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቀጠናውን አገራት በብዙ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ግዙፍ የአፍሪካ ፕሮጀክት ሲሆን ከብክለት የፀዳ፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን እውን የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።  

የግድቡ ዓላማና ጠቀሜታው ይህ ሆኖ እያለ ኢትዮጵያ ከአባይ ወንዝ ምንም አይነት ተጠቃሚነት እንዳይኖራት እየሰሩ ያሉ አገራት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ይህም የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብታዊ ጥንካሬና ከእድገቷ ጋር ሊመጣ የሚችልን የኃይል ሚዛን ሊቀይር ይችላል ከሚል ስጋት የሚመነጭ መሆኑን አብራርተዋል።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ሥራ ሲጀምር ኢትዮጵያ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን እንድታንቀሳቅስ ያስችላታል ነው ያሉት።

ለጎረቤት አገራት ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቷን በማሳደግ ከቀጠናው አገራት ጋር ተሳስራ ለማደግ ያስቀመጠችውን መርህ የሚያሳልጥ ፕሮጀክት ስለመሆኑም ተናግረዋል።

የቀጠናውን አገራት አውንታዊ ግንኙነት በማጠናከርም የማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ እንደሚያስችል አመላክተዋል።

በቀጠናው የድንበር አካባቢዎች ነፍጥ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኞችንና ጸረ ሰላሞችን በሁሉም አገራት በኩል ቦታ እንዳያገኙ እንደሚያደረግ ተናግረዋል።

የንግድ ትስስር በማጠናከር፣ የማህበረሰብ ግንኙነት በማሳደግ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታን ማስፋት፣ ዘላቂ ሰላም እና ደህንነት እንዲሰፍን ማድረግም የህዳሴው ግድብ ይዟቸው የሚመጡ በረከቶች እንደሆኑ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጧ እና ያላት ሰፊ የህዝብ ቁጥር ለዓረቡ ዓለም፣ ለኤስያ፣ ለአውሮፓ፣ ለመካከለኛው ምስራቅና ደቡባዊ የአፍሪካ ክፍል መግቢያ በር በመሆኑ ተመራጭ መዳረሻ ያደርጋታል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ለግድቡ መጠናቀቅ እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው በማስቀጠል ከግብ እንዲደርስ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም