ዳያስፖራው ባለፉት ሦስት ወራት 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት ልኳል

67

አዲስ አበባ፣ ህዳር 13/ 2014 (ኢዜአ)  ዳያስፖራው ባለፉት ሦስት ወራት 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ውስጥ መላኩን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ገለጸ ።

የኤጀንሲው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከዳያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ የሚላከው ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ለዚህም ዳያስፖራው በ2013 ዓ.ም በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት የላከውን 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ባለፉት ሦስት ወራት ከተላከው ጋር በማነጻጸር ለአብነት ጠቅሰዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ከዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ መላኩን የጠቀሱት አቶ ወንድወሰን ያሳየውን ከፍተኛ እድገት አመላክተዋል።

በሌላ በኩል በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኘው የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን የውጭ ጫና ለመከላከል የተለያዩ ጥረቶች እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ከሚያደርጋቸው ተሳትፎዎች ባሻገር በሚኖሩባቸው አገራትም በሠላማዊ ሠልፍ ጭምር እየታገለ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ እንዲረዳ በማድረግና የሚያሳድራቸውን ያልተገቡ ጫናዎች በመከላከል ረገድ ውጤታማ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

በተጓዳኝም ዳያስፖራው ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለሠብዓዊ ድጋፎችና ለዜጎች መልሶ ማቋቋም የገንዘብና የአይነት ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ ከ125 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

ለአገራዊ ፕሮጀክቶችም ከ251 ሚሊዮን ብር በላይ ኃብት ማሰባሰብ እንደተቻለ ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው በማንኛውም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎውን ለማጠናከር ከፍ ያለ ተነሳሽነት ያለው መሆኑንም አቶ ወንድወሰን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም