ቀጥታ፡

በምርት ዘመኑ እስካሁን ከ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ሰብል ተሰብስቧል

ህዳር 13/2014 (ኢዜአ) በ2013/14 የምርት ዘመን በዘር ከተሸፈነው 12 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እስካሁን ባለው ሂደት በ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ሰብል መሰብሰቡን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

ባለፉት አራት ወራት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ወጪ ንግድ ብቻ ከ157 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱንም ነው ያስታወቀው፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ በምርት ዘመኑ በዘር ከተሸፈኑ 12 ሚሊየን ሄክታር መሬት 374 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት ከ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን  ሄክታር መሬት ላይ 74 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል ነው ያሉት፡፡

የምርት መሰብሰቡ ሂደት ላይ 1 ሺህ 200 የማጫጃ ማሽኖች (የኮምባይነሮችጥ) አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪ 400 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በበጋ ወቅት ስንዴን በመስኖ ለማልማት በዕቅድ ተይዞ ወደ ተግባር መግባቱንም ተናግረዋል።

በዘር ከሚሸፈነው መሬትም 16 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ ተደራሽነት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በዚህም ወደ ተለያዩ የእስያ አገራት፣ ህንድ፣ ቻይና ፣ ጃፓን እና ቱርክ የገበያ አማራጮች በመፈለግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ ባሳለፍናቸው ቀናቶች ትውልደ -ኢትዮጵዊያን እና የኢትዮጵያ ወዶጆች ከ25 በላይ በሆኑ የዓለም አገራት ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጫና ለመቃወም ሰልፍ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም ለማሳወቅ እያደረገ ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ባለፉት አራት ወራት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ወጪ ንግድ ብቻ 157 ነጥብ 4 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ገልጸው፤ አፈጻጸሙም ከእቅዱ አንጻር 92 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ገቢውም በዋናነት ከጨርቃጨርቅ እና አልባሳት መገኘቱ ተጠቁሟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም