ምዕራባዊያን ህወሓትን የሚደግፉት ኢትዮጵያን የመበታተን አጀንዳቸውን ፈጻሚ በመሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ምዕራባዊያን ህወሓትን የሚደግፉት ኢትዮጵያን የመበታተን አጀንዳቸውን ፈጻሚ በመሆኑ ነው
ባህርዳር ህዳር 13/2014 (ኢዜአ) ምዕራባዊያን አሸባሪውንና ወራሪውን ህወሓት የሚደግፉት ኢትዮጵያን የመበታተን አጀንዳቸውን ፈጻሚ በመሆኑ ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ።
ኢዜአ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከምሁራኑ ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዷል።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህር ዶክተር ቢሰጥ አያሌው እንዳሉት እንደ ግሪሳ አገር እያጠፋ ያለው አሸባሪው ህወሓት እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ የቻለው በምዕራባውያን እገዛ ነው።
የጥፋት ሀይሉ በምዕራባውያን መንግስታትና መገናኛ ብዙሃንና ድርጅቶች እገዛና ድጋፍ እየተደረገለት ያለው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን አገር የማፈራረስ አጀንዳ ፈጻሚ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን ተናግረዋል።
አሸባሪው ህወሃት ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነትና ፍላጎት፣ ለአገር ሉአላዊነትና ጥቅም ደንታ የሌለው መሆኑን ጠቁመው፣ "በህዝቦች ትግል ወደ አጣው ስልጣን እንዲመለስ በምዕራባዊያን ሁሉን አቅፍ ድጋፍ እየተደረገለት ነው" ብለዋል።
ምአራባዊያን በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት አሉታዊ ዘመቻ የመገናኛ ብዙሃንን ስነ ምግባርና መርሆ ያልተከተለና በሃሰት መረጃ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑም ከሳምንት በፊት "አዲስ አበባ ተከባለች" ተብሎ የተዘገበውን ዘገባ ዶክተር ቢሰጥ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
"ይሄ ዘገባ አሁን ኢትዮጵያ በተጨባጭ ካለችበት ሁኔታ ጋር አያይዤ ስመለከተው በሃሰተኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ፍጹም ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን ማረጋገጥ ችያለሁ" ሲሉም አክለዋል።
የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሀን አካሄድ በ1ኛው እና በ2ኛው የዓለም ጦርነት ጀርመኖች በሃሰት መረጃ ሰዎችን በማዋከብ እውነት ነው ብለው እንዲቀበሉ ሲያደርጉበት የነበረ የፕሮፓጋንዳ ስልት መሆኑንም ጠቁመዋል።
አሁን ሀገርና ህዝብ የገጠማቸውን አደጋ ለመመከት በችግሩ ልክና አይነት ለመመለስ መንቀሳቀስ እንደሚገባ የገለጹት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን መምህር አቶ ሞገስ አብርሃ ናቸው ።
"የምዕራቡ ዓለም መንግስታት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ ምሁራን፣ ተቋማትና ለጋሽ ድርጅቶች ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ገጽታ በማበላሸት የተጠመዱበት ወቅት ላይ እንገኛለን" ብለዋል።
ወራሪና አሸባሪውን ህወሓት ደግፈው የኢትዮጵያን ስም የሚያጠለሹ አካላትን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛውን መረጃ በወቅቱ ለህዝብ በማድረስ መመከት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የሀገር ደህንነት አደጋ ላይ ወድቆ በመደበኛው የኮሚኒኬሽን ስርዓት ውጤታማ መሆን ስለማይቻል ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ክልሎችንና ምሁራንን ያሳተፈ ቡድን አቋቁሞ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
"ሀሰተኛ መረጃ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይም በስፋት እየተሰራጨ ያለበት ወቅት ነው" ያሉት አቶ ሞገስ፣ ህወሓት በሀገራችን ከለኮሰው ጦርነት ጋር ተያይዞ ችግሩ በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸዋል።
አሸባሪው ህወሓትና አጋሮቹ በለቀቁት ሃሰተኛ መረጃም ሰዎች ከቄያቸው መፈናቀላቸውንና ለኢኮሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች ቀውሶች መጋለጣቸውን አስገንዝበዋል።
አቶ ሞገስ እንዳሉት የምዕራቡ ዓለም የሚያዩት ምን አይነት መረጃ ተሰራጨ የሚለውን ሳይሆን የጩኸቱን ብዛት ብቻ ነው።
በዚህም ተጨባጭ ነገር በሌለበት ሁኔታ ለማስተካከል በሚል ወደ ርምጃ የሚገቡበትና የበለጠ ቀውስ የሚፈጠርበት ሁኔታ እንዳለ አስታውሰዋል።
በመሆኑም የህወሓት የጥፋት ሀይል በጋሊኮማ፣ ጭና፣ አጋምሳ፣ ማይካድራና ሌሎች አካባቢዎች በንጹሀን ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋና ሌሎች ግፎች በተከታታይነት ማጋለጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በተለይ ትዊተር የሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያንና በተለያዩ ሀገራት ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በተናበበና በተጠና ሁኔታ የአገራቸውን ትክክለኛ ገጽታ ማሳየት እንዳለባቸው ነው አቶ ሞገስ ያስገነዘቡት።