ቀጥታ፡

የጭሮ ከተማ ወጣቶች ለሕልውና ዘመቻው ስኬት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረጉ ነው

ጭሮ ፤ህዳር 12 /2014 (ኢዜአ) የጭሮ ከተማ ወጣቶች ለሕልውና ዘመቻው ስኬት አዲስ ንቅናቄ ጀምረው እየሰሩ መሆናቸውን የከተማው ወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የከተማው ወጣቶች ሉዓላዊነትን ለማስከበር በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ለሚደረገው ሁለገብ ድጋፍ በዚህ ሳምንት አዲስ ንቅናቄ  ጀምረዋል።

የጭሮ ከተማ የወጣቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብሮ አብደላ እንደገለጹት የከተማዋ ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሰራዊቱን  ለመደገፍ በተጀመረው ንቅናቄ እስካሁን ከ50 ሺህ ብር በላይ አሰባስበዋል፡፡

ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር በማህበረሰብ ፖሊስ አገልግሎት ተሰማርተው አካባቢያቸውን ከአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ሰርጎ ገቦች እየጠበቁ ነው ብለዋል፡፡

የከተማው ወጣቶች  በመርህ ከተቀመጡት የጠብቅ፣ ዝመት፣ ደግፍ አላማን በማሳካት ላይ  አጠናክረው  እየሄዱ እንደሚገኙም ኃላፊው አክለዋል፡፡

የከተማዋ ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ መሀመድ እንዳሉት የከተማው ወጣቶች  በሀገራቸው ጉዳይ ላይ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ነው።

አክለውም ወጣቶች ከተደራጁ  በትክክል የለውጥ ኃይል መሆናቸውን በአንድ ሳምንት ስራ አስመስክረዋል ብለዋል፡፡

ከንቅናቄው ተሳታፊዎች አንዱ የሆነው  ወጣት ሽኩር መሀመድ  የጭሮ ወጣቶች የሀገርን ህልውና በማስቀጠል ረገድ  ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው ብሏል።

ሀገርን በአሸባሪዎች ከተደቀነባት ወቅታዊ የሕልውና አደጋ  መታደግ  የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት  ቢሆንም  ከወጣቶች ብዙ ይጠበቃል።

በመሆኑም ወጣቶች በሙሉ አቅማቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታ እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሀገር ለማፍረስ እኩይ ዓላማ እንግበው የተነሱትን አሸባሪዎቹ  ህወሓትና ሸኔ  ዳግም የሀገር ስጋት እንዳይሆኑ እተደረገ ላለው ትግል ወጣቶች ሁለንተናዊ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ አሳስቧል፡፡

ወጣት ኢፍቱ መሀመድ በሰጠችው አስተያየት "የጭሮ ወጣቶች የሰላማችን ኃይል ከሆነው መከላከያ ሠራዊት ጎን ለመሰለፍ  ሁላችንም በአንድነት መንፈስ ቆመናል" ብላለች፡፡

ወጣቷ የአካባቢን ሰላም በማስፈን  ከሚደርሱ የፀጥታ ችግሮች  አስቀድሞ ለመከላከል  በሚደረገው ጥረትም ሆነ በሕልውና ዘመቻው በሀገር ፍቅር ስሜት እየተሳተፈ መሆኑን ጠቅሳለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም