ለአገር ህልውና ህይወቱን እየሰጠ ላለው ሰራዊት ደማችንን ሰጥተናል - ኢዜአ አማርኛ
ለአገር ህልውና ህይወቱን እየሰጠ ላለው ሰራዊት ደማችንን ሰጥተናል
ህዳር 12/2014 (ኢዜአ) የተክለሃይማኖት ሰፈር አብሮ አደግ በጎ አድራጎት መርጃ ማህበር አባላት የአገርን ሉዓላዊነትና ህልውና ለማስከበር በግንባር እየተፋለመ ለሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ደም ለግሰዋል፡፡
የማህበሩ ሊቀንበር አቶ በረከት ተሾመ "ዛሬ ላይ በሰላም ወጥተን የምንቀሳቀሰው ዋጋ እየከፈለልን ባለው ሰራዊታችን ነው" ብለዋል፡፡
በመሆኑም "ህይወት ለሚሰጥ ደም መስጠት ቢያንስ እንጂ አይበዛምና" የኢትዮጵያ መከታ ሆኖ ለቆመው ሰራዊታችን ደማችንን ለግሰናል ነው ያሉት።
ማህበሩ ከመከላከያ ጎን ቆሞ የተቻለውን ለማድረግ ሁሌም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠው ለአገራችን ህልውና ሁላችነም በጋራ የምንቆምበት ጊዜ አሁን ነው ብለዋል።
ደማቸውን ሲለግሱ ያገኘናቸው የማህበሩ አባል አቶ ስለሽ ታደሰ "ለአገሬ አቅሜ የፈቀደውን የማላደርግበት ምንም አይነት ምክንያት የለም" ሲሉ ተናግረዋል።
"የመኖር፣ ትውልድ የማስቀጠልና የሁሉም ነገር መሰረታችን ኢትዮጵያ ነች፤ ሊያፈርሷት ከተነሱት ሃይሎች ልንታደጋት ይገባል" ብለዋል፡፡
ከአብሮ አደግ በጎ አድራጎት መርጃ ማህበር ጋር በመሆን በቀጣይም አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውነም አረጋግጠዋል።
ከደም ለጋሾቹ መካከል ወይዘሮ ትዕግስት ደምሴ፤ በበኩላቸው በማህበራቸው ስም ደም በመለገስ የድርሻቸውን በማበርከታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
የደም ልገሳ ከመልካምነት መገለጫዎች መካከል አንዱ በመሆኑ ይህ ደግሞ ከአብሮ አደግ በጎ አድራጎት መርጃ ማህበር ግብና አላማ ጋር አብሮ የሚሔድ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዛሬ ሶስት አመት በፊት የተመሰረተው የተክለሃይማኖት ሰፈር አብሮ አደግ በጎ አድራጎት መርጃ ማህበር ጧሪ የሌላቸው አረጋውያንና የጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን እየረዳ ይገኛል።