ቀጥታ፡

የፖሊስ አባላት ወቅታዊ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን በብቃት ለመፈፀም ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል

ሀዋሳ ፤ህዳር 11/2014(ኢዜአ) የፖሊስ አባላት ለለበሱት የደንብ ልብስ ተገቢውን ክብር መስጠትና ወቅታዊ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን በብቃት ለመፈፀም መዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው ተመለከተ ፡፡

የሲዳማ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የአባላት የደንብ ልብስ ለውጥ ዛሬ ይፋ አደረገ።

በመርሀ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዋና ዐቃቤ ሕግ መቶ ማሩ እንዳሉት፤ የአባላት የደንብ ልብስ ለውጥ እየተተገበረ ያለው የተቋማዊ ሪፎርም አንዱ አካል ነው።

ከደንብ ልብስ ለውጡ ባሻገር የሪፎርም ሥራው ከዚህ በፊት በሕግ ጥላ ሥር ባሉ ግለሰቦች የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አያያዝ ላይ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ለመፍታትም  እንደሆነ ተናግረዋል።

የፍትሕ ተቋማትን የማደራጀትና አባላቱን የማብቃት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፖሊስ አባላት በአመለካከትም ጭምር በመታደስ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ያሉት ዋና ዐቃቤ ሕጉ፤  ለለበሱት የደንብ ልብስ ተገቢውን ክብር መስጠትና ወቅታዊ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን በብቃት ለመፈፀም ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

ሀገራዊ የክተት አዋጁን ተከትሎ በማንኛውም ወቅት መንግስት ለሚያደርግላቸው ጥሪ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅተው መጠበቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር ኮንታሞ ቡርቃ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት የነበረው የተቋሙ የደንብ ልብስ ካለበት የጥራት ችግር ባለፈ በግለሰቦች እጅ የሚገኝና ፀረ-ሠላም ኃይሎች ለሽብር ተግባር እያዋሉት ያለ በመሆኑ ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።

የተቋሙ የፖሊስ አባላት ሙያዊ ተግባራቸውን በትጋት ከመፈፀም ባሻገር ወራሪውን ኃይል በቆፈረው ጉድጓድ ለመቅበር የሚደረገውን የህልውና ዘመቻ ለመቀላቀል  ተዘጋጅተው መጠባበቅ አለባቸው ብለዋል።

ከኮሚሽኑ ፖሊስ አባላት መካከል ረዳት ሳጅን ብዙነሽ በራሳ በሰጡት አስተያየት፤  ከደንብ ልብሳችን ጋር አመለካከታችንም ሊቀየር ይገባል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ የደንብ ልብሱን የሚመጥን ሥራ በማከናወን ፖሊሳዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ ነው የገለጹት።

ምንጊዜም ቢሆን ሀገራዊ ጥሪ ቢደረግላቸው ያለማመንታት ተቀብለው በመዝመት በግንባር ጀብድ እየፈፀሙ የሚገኙ ሴት እህቶቻችንን ገድል እንደግማለን ብለዋል።

ዋና ኢንስፔክተር ሰለሞን ለገሰ ፤ እንደ ሀገር ማንኛውንም ተልዕኮ በመፈፀም የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኮሚሽኑን መደበኛ ሥራዎች በአግባቡ ከመፈፀም ባለፈ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለመታደግ ለሚደረገው ዘመቻ ጥሪ ተቀብለን ወደ ግንባር ለመዝመት በአካልም ሆነ በሥነ-ልቦና ተዘጋጅተን እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም