ቀጥታ፡

የተዘረፉ ቅርሶችን ለማስመለስ ከመንግስት ጥረት ባሻገር የኢትዮጵያውያንና ትውልደ -ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ ይጠይቃል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የወጡ ቅርሶችን ለማስመለስ ከመንግስት ጥረት ባሻገር የኢትዮጵያውያንና ትውልደ -ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ተናገሩ።

ከዛሬ 153 ዓመት በፊት በመቅደላ በተካሄደው ጦርነት ተዘርፈው የወጡ 13 ቅርሶች ከእንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ ዛሬ ተመልሰዋል፡፡     

የእጅ መስቀል፣ ዘውድ፣ የጸሎት መጽሃፍት፣ መጠጫዎች እና የተለያዩ ሃይማኖታዊ ቅርሶች ከተመለሱት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ቅርሶቹን ለማስመለስ በታላቋ ብሪታኒያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ኮሚቴ፣በብሪታኒያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ተገልጿል።        

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እንደተናገሩት፤ቅርሶችን ለማስመለስ የተቀናጀ ዲፕሎማሰያዊ ጥረት ተደርጓል።

በተጨማሪ የሼህ ራዛድ ፋውንዴሽ መስራች ታሂር ሻህ፣ምሁራን፣ያገባናል የሚሉ ግለሰቦች ላደረጉት ርብርብ በሚኒስቴሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤት መሆኗን ቅርሶቿ ህያው ምስክር ናቸው ሲሉም አክለዋል።

የተለያዩ የኢትዮጵያ ቅርሶች በህገ-ወጥ መንገድ ከአገር ወጥተው በተለያዩ አገራት ሙዚዬሞች፣በጥናት ተቋማትና በግለሰቦች እጅ እንደሚገኙም ተናግረዋል።   

እነዚህን ቅርሶች ለማስመለስ መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ የኢትዮጵያውያን ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

በታላቋ ብርታኒያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተፈሪ መለስ በበኩላቸው በመቅደላ ጦርነት ወቅት ከኢትዮጵያ ተዘርፈው የሄዱ በርካታ ቅርሶች በእንግሊዝ እንደሚገኙ አስታውሰዋል።

ቀሪ ቅርሶችን ለማስመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርሶች መመለስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ገጽታ በመገንባት ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው  ተናግረዋል፡፡

"በብርታኒያ ሙዚዬም የሚገኙ አስራ ሁለት የሚጠጉ ታቦታት ለማስመለስ ድርድር ተጀምሯል፤ በቅርብ ጊዜ ይሳካልናል ብለን እናምናለን" ነው ያሉት።   

የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር አሉላ ፓንክረስት በበኩላቸው ሼህ ራዛድ ፋውንዴሽን ለጨረታ ሊቀርቡ የነበሩ በርካታ ቅርሶችን በማስመለስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል፡፡    

ከብርታኒያ መንግስት ጋር በተደረገ ድርድርና ጥረት ከሁለት ዓመት በፊት የአጼ ቴዎድሮስ ጸጉር (ቁንዳላ)  ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ ይታወሳል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም