ቀጥታ፡

ባለቤቴ ሀገርን ለማዳን ወደ ግንባር ከሄደ ጀምሮ የማህበረሰቡ እገዛ አልተለየኝም

መተማ ፤ ህዳር 11/2014(ኢዜአ) ባለቤቴ ሀገርን ለማዳን የቀረበለትን የክተት ጥሪ በመቀበል ወደ ግንባር ከሄደ ጀምሮ የአካባቢው ማህበረሰብ እገዛ እንዳልተለያቸውም የዘማቹ ባለቤት ይናገራሉ።

ወይዘሮ ግርማለች ገለጠው በምዕራብ ጎንደር መተማ ወረዳ የኮኪትና  ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ ባለቤታቸው ከአካባቢው ወደ ግንባር ከዘመቱ  የሚሊሻ  አባላት መካከል አንዱ ናቸው።

የመተማ ወረዳ የመንግስት ሰራተኞች  በወረዳው  ቀበሌዎች  የክተት ጥሪውን ተቀብለው ግንባር የተሰለፉ የሚሊሻ አባላት ሰብል ሰብስበዋል።

ሰብላቸው ከተሰበሰበላቸው ውስጥ ወይዘሮ ግርማለች፤  ባለቤቴ ሀገርን ለማዳን   ወደ ግንባር በመሄዱ ኩራት ይሰማኛል ነው ያሉት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት።

ባለቤቴ ወደ ግንባር ከሄደ ጀምሮ  የአካባቢው ማህበረሰብ ተገቢው እገዛ  አልተለየኝም ያሉት ወይዘሮዋ፤  አሁን ደግሞ  በሶስት ሄክታር መሬት የለማ የጤፍ ሰብል ብክነት ሳይደርስ በመሰብሰቡ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

''ከዚህ ቀደምም ለልጄ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጎልኛል'' ያሉት ወይዘሮ ግርማለች፤  በህዝቡና መንግስት ሰራተኛው የተደረገላቸው ድጋፍ  የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው ልጃቸውን ያዘመቱት አርሶ አደር ጌጡ ለገሰ በበኩላቸው፤  በሁለት ሄክታር የለማው የጤፍ ሰብል በመንግሥት ሰራተኞች እንደተሰበሰበላቸው ነው የገለጹት።

''ልጄ ወደ ግንባር ሲሄድ ቅር አላለኝም፤ ምክንያቱም እኔና መላ ቤተሰቡን ሊጠብቅ መሄዱን ስለማውቅ ነው'' ብለዋል።

በሰራተኞቹ የተደረገላቸው ድጋፍ የጉልበት ሰራተኛ ቢጠቀሙ ከ3 ሺህ ብር በላይ ሊያስወጣቸው የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ እና አስተዳደርም በየጊዜው ምን እንደሚያስፈልጋቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበላቸው ከጎናቸው እንደሆነም አመልክተዋል።

የመተማ ወረዳ መምህራን ማህበር ሊቀመንበር ሙሉጌጡ መርሻ እንዳሉት፤ የክተት ጥሪውን ተቀብለው ግንባር የተሰለፉ ዘማቾችን ሰብል መሰብሰብ የህብረተሰቡ ድርሻ ነው።

''የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ጠላት የሆነውን አሸባሪ ቡድን ለመደምሰስ ግንባር የዘመቱ ዘማች ቤተሰቦችን አለንላችሁ ልንል የግድ ነው'' ብለዋል።

መማርም ሆነ ማስተማር  የሚቻለው ሀገርና ህዝብ ሲኖር በመሆኑ ሀገርን ለመጠበቅ ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

ለህልውና ዘመቻው ግንባር የዘመቱ ቤተሰብን መደገፍ መላ ህዝቡን መደገፍ ነው ያሉት ደግሞ በሰብል አሰባሰቡ ስራ ላይ ከተሳተፉ የመንግስት ሰራተኛ መካከል  አቶ ተስፋሁን አቤ ናቸው።

የህዝቡን ሰላም ለመጠበቅ ግንባር ለተሰለፉ ዘማች ቤተሰቦች ያልተቋረጠ ድጋፍ ማድረግ የሁሉም ግዴታ እንደሆነ ተናግረዋል።

በወረዳው ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች ወደ ግንባር የሄዱ ሚሊሻና አርሶ አደሮችን ማሳ የመንግስት ሰራተኛው እና ማህበረሰቡ እየሰበሰበ ነው ያሉት ደግሞ የመተማ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ አህመድ ናቸው።

በዘመቻው በቀን 300  የሚደርስ የሰው ኃይል በተለያዩ የዘማች አርሶ አደር ማሳ በመሰማራት የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተካሄደ የሰብል ስብሰባም ከ70 ሄክታር በላይ የጤፍና የማሽላ ሰብል መሰብሰብ እንደተቻለ  ገልጸዋል።

በቀጣይም የመንግስት ሰራተኞችንና ማህበረሰቡን በማስተባበር 700 ሄክታር በላይ ሰብል የመሰብሰብ ስራ ይሰራል  ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም