ቀጥታ፡

ምዕራባውያን ሚዲያዎች የተዛቡ ዘገባዎችን የሚያሰራጩት አሸባሪው ህወሃት ተመልሶ ስልጣን እንዲይዝ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ)አንዳንድ ምዕራባውያን ሚዲያዎች የተዛቡ ዘገባዎችን የሚያሰራጩት አሸባሪው ህወሃት ተመልሶ ስልጣን እንዲይዝ ካላቸው ፍላጎት የመነጨ መሆኑ ተገለጸ፡፡

እነዚህ ሚዲያዎች ዘገባዎቻቸውን የሚሰሩት በሰብዓዊነት ሽፋን የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ነውም ተብሏል፡፡

የኪንግ ኦፍ አባይ ሚዲያ መስራችና የህዳሴ ግድብ ተሟጋች ዑስታዝ ጀማል በሽር እንዳሉት፤ የምዕራባውያን ሚዲያዎች ለአንድ ወገን ያጋደለ ዘገባ የሚያሰራጩት ኢትዮጵያ ውስጥ "ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት” የሚል ተላላኪ መንግስት እንዲመሰረት ካላቸው ፍላጎች የተነሳ ነው፡፡

ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ፓርላማ በአሸባሪነት የፈረጀውን ህወሃት ምርጫቸው አድርገዋል ብለዋል፡፡

አሸባሪው ህወሃት በጦር ግንባር የደረሰበትን ሰብዓዊ አና ቁሳዊ ኪሳራ በፕሮፖጋንዳ ለማካካስ አይን ባወጣ የሃሰት ዘገባ ሌት እና ቀን ሳይታክቱ ሲሰሩለት ይስተዋላል ብለዋል፡፡

ይህን ከተማ ተቆጣጠሩ፣ ከዚህ ቦታ ደረሱ እያሉ የሃሰት ዘገባ በመስራት ህዝቡን በማሸበር የመኖሪያ ቀየውን ለቆ እንዲወጣ የማድረግ ስራ ይሰራሉ ብለዋል፡፡

ይህን ስትራቴጂ የሚጠቀሙት በህዝቡ ላይ አንድም የስነ ልቦና ጫና ለማሳደር ሁለትም የመኖሪያ ቀየውን ለቆ ሲወጣ ለመዝረፍ እንዲያመቸው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ዑስታዝ ጀማል "ከአሜሪካ ኢትዮጵያ እንደገባሁ የተለያዩ ቦታዎችን ተዘዋውሬ አይቻለሁ፤ ምንም አይነት ስጋት የሚሆን ነገር የለም፤ የምዕራባዊያን ሚዲያዎች የሚዘግቡት ዘገባ ፍጹም ውሸት መሆኑን አረጋግጫለሁ ነው "ያሉት፡፡

እነዚህ ሚዲያዎች የሚያሰራጩትን የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ቀድሞ በመዘገብ ህብረተሰቡ እንዳይደናገር ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ህዝቡ ደግሞ ለአሸባሪው ግልጽ የሆነ አድሎ ለሚታይባቸው የውጭ ሚዲያዎች ጀሮ ባለመስጠት ከመንግስት የሚወጡ መረጃዎችን ብቻ መውሰድ እንዳለበትም መክረዋል፡፡

የኢትዮ-አረብ ግንኙነት ተመራማሪ ዛሐድ ዚዳን በበኩላቸው መላው ኢትዮጵያዊያን ለነዚህ "ወደቀ ሲሉ ተሰበረ፤ ታመመ ሲሉ ሞተ" እያሉ ለሚዘግቡ የውጭ አገር ሚዲያዎች ጀሮ መስጠት እንደሌለበት ገልጸዋል፡፡

የእነዚህን ሚዲያዎች እኩይ አላማ ለመቀልበስ መንግስትና ህዝብ ተቀናጅተውና ተናበው መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

-አካባቢህን ጠብቅ _

ወደ ግንባር ዝመት _

መከላከያን ደግፍ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም